የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኮላቦሬሽን ኦን ኢንተርናሽናል አይሲቲ ፖሊሲ ፎር ኢስት ኤንድ ሳውዘርን አፍሪካ (Collaboration on International ICT Policy for East and Southern Africa) ከተባለ ድርጅት ጋር በመተባበር የዲጂታል መብቶችን በተመለከተ ለኮሚሽኑ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች ባለሙያዎች መስከረም 30 እና ጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ሁለት ቀናት በቆየው ስልጠና ስለ ዲጂታል መብቶች፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እድገት ምክንያት በሰብአዊ መብቶች ላይ ስለተፈጠሩ አወንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖዎች በተመለከተ ውይይት ተደርጓል፡፡ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት፣ የተሳሳተ መረጃን ላልተገባ ጥቅም ማዋል እንዲሁም መሰል ተግዳሮቶች እና መፍትሔዎቻቸው በውይይቱ ተዳሰዋል። በተጨማሪም ኮሚሽኑ ከተሰጠው ሥልጣን አንጻር የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር እያካሄደ ስላለው ሥራ እና ይህንኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል ስለሚያስችሉ ዕድሎች ውይይት ተደርጓል።

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል የዲጂታል ቴክኖሎጂ መተዋወቅ በአንድ በኩል ለሰብአዊ መብቶች ሥራ በጎ አስተዋጽዖ አድርጓል በሌላ በኩል የዲጂታል ቴክኖሎጂ እድገት የሰዎችን የግል ሕይወት እና እንቅስቃሴን የተመለከቱ መረጃዎችን ያለፍላጎታቸው መከታተል እንዲቻል በማድረጉና በሌሎች መሰል ምክንያቶች የሰብአዊ መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩን ገልጸዋል። በመሆኑም አሉታዊ ተጽዕኖዎቹን በመቀነስ ዲጂታል ቴክኖሎጂን ለሰብአዊ መብቶች ማስፋፋት እና ማስከበር ሥራ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።