የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የኦሞ ወንዝ ከመጠን በላይ በመሙላቱ እና መደበኛ የመፍሰሻ መስመሩን ለቆ በመውጣቱ ምክንያት በጎርፍ ከተጥለቀለቁ የወንዙ የታችኛው ተፋሰስ አካባቢዎች በተለይም ከዳሰነች ወረዳ የተፈናቀሉ ሰዎችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አስመልክቶ ከጥቅምት 5 እስከ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ክትትል በማከናወን ያዘጋጀውን ባለ 26 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡

ኢሰመኮ የክትትል ሥራውን ሲያከናውን በቡድን ውይይት፣ በቃለ መጠይቅ፣ በሰነድ ምርመራ እና በመጠለያ ጣቢያዎች ላይ የአካል ምልከታ በማድረግ መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን አሰባስቧል፡፡ ከተፈናቃዮች ጋር የጾታ፣ የዕድሜ እና የአካል ጉዳት ሁኔታ ስብጥርን ታሳቢ ያደረጉ 6 የቡድን ውይይቶችን፣ እንዲሁም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው 11 የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ከ5 መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅቶች እና ከሲቪል ማኅበራት ተወካዮች ጋር ውይይቶችን እና ቃለ መጠይቆችን አድርጓል። በተጨማሪ የክትትሉን ግኝቶች ለማጋራት፣ በክትትሉ በተለዩ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አሳሳቢ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች እና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ለመወያየት እንዲሁም ምክረ ሐሳቦቹ እንዲፈጸሙ ለመወትወት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በተለያዩ ጊዜያት የምክክር መድረኮችን አካሂዷል።

የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሪፖርቱ በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ውስጥ ባሉ 12 የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አግባብነት ካላቸው ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ሕጎችና ሰነዶች አንጻር የገመገመ ሲሆን፣ የመፈናቀል መንስኤዎችን፣ በመፈናቀል እና ድኅረ መፈናቀል ወቅት የደረሱ ጉዳቶችን እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እና አሳሳቢ ሁኔታዎችን ለይቷል፡፡

በላይኛው የኦሞ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢዎች በክረምት ወራት የሚዘንበው ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ የኦሞ ወንዝ ከመጠን በላይ እንዲሞላ እና መደበኛ የመፍሰሻ መስመሩን ለቆ እንዲወጣ ማድረጉ፤ በ2012 ዓ.ም. የክረምት ወቅት የግልገል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ግድብ በመሙላቱ ምክንያት ግድቡን ለማስተንፈስ የተለቀቀው ውሃ የኦሞ ወንዝ በከፍተኛ መጠን እንዲሞላ እና ወንዙ ከዚህ ቀደም በጎርፍ ከሚያጥለቀልቃቸው ቦታዎች በተጨማሪ በሌሎች ቦታዎች ላይ የጎርፍ አደጋ እንዲከሰት አስተዋጽዖ ማድረጉ፤ እንዲሁም የወንዙን በከፍተኛ ሁኔታ መሙላት ተከትሎ የቱርካና ሐይቅ በኅዳር ወር 2013 ዓ.ም. ከመጠን በላይ መሙላቱና ወደ ሐይቁ የሚገባው ውሃ ወደ ኋላ መመለስ መጀመሩ (back flooding) በአካባቢው ያደረሰው ጉዳት የመፈናቀሉ መንስኤዎች ናቸው።

የኦሞ ወንዝን በከፍተኛ ሁኔታ መሙላት እና የዳሰነች ወረዳ በርካታ አካባቢዎችን በጎርፍ መጥለቅለቅ ተከትሎ፣ ሰዎች ለመፈናቀል ከመዳረጋቸው ባሻገር፣ በሕይወታቸው፣ በአካላቸው፣ በንብረታቸው እንዲሁም ትምህርት እና ጤናን ጨምሮ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን በሚያገኙባቸው ተቋሟት ላይ  ጉዳት የደረሰ መሆኑን የክትትል ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም ሪፖርቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአንዳንድ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ መሻሻሎች ቢኖሩም፣ የተፈናቃዮችን የመመዝገብ እና ሰነድ የማግኘት መብት፣ ደኅንነቱ እና ጸጥታው በተረጋገጠ ሁኔታ የመኖር መብት፣ በተቻለ መጠንና ፍጥነት የምግብ፣ የውሃ፣ የመጠለያ፣ የሕክምና እና ሌሎች የጤና አገልግሎቶች፣ የንጽሕና፣ የትምህርት እና ሌሎች አስፈላጊ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ያካተተ በቂ የሰብአዊ ድጋፍ የማግኘት መብት፣ እንዲሁም ልዩ ጥበቃ እና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ተፈናቃዮች አያያዝ በተመለከተ ክፍተቶች መኖራቸውን ያሳያል። የክትትል ሪፖርቱ ተፈናቃዮችን በቋሚነት በማቋቋም ረገድ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት በኩል አበረታች ጥረቶች የተጀመሩ መሆናቸውንም ይገልጻል።

ኢሰመኮ በሰብአዊ መብቶች ክትትሉ የለያቸውን ክፍተቶች መሠረት አድርጎ በተለይም ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአስተዳደር፣ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር፣ የወሳኝ ኩነት፣ የትምህርት እና የጤና መዋቅሮች እንዲሁም ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ልዩ ልዩ ምክረ ሐሳቦችን አቅርቧል። በዚህም መሠረት ልዩ ድጋፍ የሚሹ ተፈናቃዮችን ቅድሚያ በሰጠ መልኩ ለተፈናቃዮች በቂ፣ ወቅቱን የጠበቀ እና ተደራሽ ሰብአዊ ድጋፍ የማቅረቡ ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ የክልሉ በየደረጃው ያሉ የጤና መዋቅሮች ከሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር ተቀናጅተው ተፈናቃዮች ነጻ የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበትን፣ በሁሉም የተፈናቃይ መጠለያዎች የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት የሚካሄድበትን እንዲሁም የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር የሚቀርብበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ፤ እንዲሁም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚያደርገው ጥረት ተፈናቃዮች በሚገባ መሳተፋቸውን እንዲያረጋግጥ ኢሰመኮ በሪፖርቱ አሳስቧል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ስምምነት (የካምፓላ ስምምነት) አባል ሀገር እንደመሆኗ መንግሥት በስምምነቱ የተጠበቁ መብቶችን በተቻለ መጠን እና ፍጥነት የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን አስታውሰው፣ “በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት የሚከሰት መፈናቀልን ለማስወገድ እና መፈናቀል ሲከሰትም የሰብአዊ መብቶች መርሖችን የተከተለ ዘላቂ መፍትሔ ለማመቻቸት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሠሩ ይገባል” ብለዋል።