የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ደቡብ ኦሞ ዞን፣ ዳሰነች ወረዳ እንዲሁም በአሪ ዞን የሚገኙ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ያለበትን ሁኔታ ለመረዳት ከጥቅምት 5 – 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ባከናወነው ክትትል በለያቸው ግኝቶች እና ባቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ጥር 2 ቀን 2016 ዓ.ም. በዎላይታ ከተማ ተወያይቷል፡፡ በውይይቱ የፌዴራል፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የደቡብ ኦሞ ዞን፣ የዳሰነች ወረዳ እና የአሪ ዞን የመንግሥት አካላት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በውይይቱ ኮሚሽኑ በኦሞ ወንዝ ሙላት ምክንያት እንዲሁም በአሪ ዞን በግጭት የተነሳ የተፈናቀሉ ሰዎች የሚገኙባቸው 11 የተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ባከናወነው ክትትል የለያቸው ግኝቶች እና የሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል። በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ በአጠቃላይ 79,828 የተመዘገቡ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መኖራቸው፤ የኦሞ ወንዝ ሙላት አለመቀነሱ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ የውሃው መጠን መጨመሩ በተወሰኑ መጠለያ ጣቢያዎች በሚገኙ ተፈናቃዮች ላይ ሥጋት ማሳደሩ፤ በወረዳው ካሉ 40 ቀበሌዎች 28ቱ በውሃ በመሸፈናቸው በማሳ የነበሩ ሰብሎች እንዲሁም የቤት እንስሳት በውሃ መወሰዳቸው ተገልጿል። በመጠለያ ጣቢያዎቹ ላሉ ተፈናቃዮችም በቂ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ የሕክምና እንክብካቤ እና ሌሎች የጤና አገልግሎቶች እየቀረበላቸው እንዳልሆነ ክትትሉ አሳይቷል።

በውይይቱ የተገኙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሥሪያ ቤት ተወካይ የግልገል ጊቤ 3 ኃይል ማመንጫ ግድብ በኦሞ ወንዝ ላይ የተገነባ በመሆኑ ወደፊት በዳሰነች ወረዳ በወንዙ ዳርቻ የሚኖሩ ሰዎች እንዳይጎዱ ለማድረግ ጥናት እያስጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአሪ ዞን አስተዳዳሪ በበኩላቸው በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቀድሞ የመኖሪያ አካባቢያቸው ለመመለስ የተጀመረው የቤቶች ግንባታ በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ እና ተፈናቃዮችን የመመለስ ሥራ የሚከናወን መሆኑን አስረድተዋል። መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅቶች ተወካዮች፤ ለተፈናቃዮች ሰብአዊ ድጋፍ መስጠት ለተወሰኑ ወራት ብቻ የሚከናወን የአጭር ጊዜ ምላሽ (emergency response) መሆኑን አስታውሰው የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት መርኃ ግብር በመንደፍ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ በአብሮነት ሊሠሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይ በውይይት መድረኩ የተገኙ ሌሎች የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሥራ ኃላፊዎች፤ በክትትሉ የተለዩ ግኝቶች ተፈናቃዮች የሚገኙበትን ሁኔታ የሚገልጽ መሆኑን ገልጸው፣ በዳሰነች ወረዳ የሚገኙ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም በክልሉ መንግሥት አቅጣጫ ተይዞ ለሁሉም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የሥራ ክፍፍል መደረጉንና ዕቅድ መውጣቱን አስረድተዋል። የቀረቡትን ምክረ ሐሳቦች መተግበር እንዲችሉ የድርጊት መርኃ ግብር ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን፣ ይህንኑም በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለመፈጸም እና ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ተስማምተዋል።

የኢሰመኮ የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና የፍልሰተኞች መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር እንጉዳይ መስቀሌ፣ በተለያየ ምክንያት ከመኖሪያ አካባቢያቸው ተፈናቅለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ እና በመጠለያ ጣቢያዎችም እያሉ በቂ የምግብ፣ የውሃ፣ የመጠለያ እና የጤና አገልግሎቶች እንዲቀርቡላቸው ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።