የባለሙያ አስተያየት ከኢሰመኮ
ዮርዳኖስ ባህሩ
የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል
የሰብአዊ መብቶች ባለሙያ

ዲስሌክሲያ በቋንቋ ላይ የተመሠረተ የመማር እና የማንበብ ችሎታዎች እድገት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድር እና ከነርቭ መዛባት (Neurological Disorder) የሚመነጭ እክል ነው። እንደ ኢንተርናሽናል ዲስሌክሲያ  ማኅበር  ዲስሌክሲያ  በቋንቋ  ላይ  የተመሠረተ የመማር  እክል እንጂ የአካል ወይም እድገታዊ ጉዳት (developmental disability) አይደለም[1]፡፡ ዲስሌክሲያ ያለባቸው ሰዎች በትክክል እና አቀላጥፈው ያለማንበብ፣ የፊደል ቃላትን አዟዙሮ የማንበብ፣ ያልተጻፈውን በግምት የማንበብ፣ የፊደሎችን ስም የሚወክሉትን ድምጽ ለመለየት መቸገር፣ በተለይ ተመሳሳይ የሆኑ ፊደላትን ማዟዟር ወይም መገልበጥ፣ ተቀራራቢ ቅርጽ ያላቸውን ፊደላት መለየት መቸገር ለምሳሌ፦ እና ቡ፣ እና ሳ፣ b እና d ፣ p እና q ወዘተ አቀያይሮ መጻፍ የመሳሰሉ ከንባብ እና ከቋንቋ ጋር የተገናኙ ተግዳሮቶች ይገጥሟቸዋል፡፡

ዲስሌክሲያ ከአእምሮ ምጥቀትም (Intelligence Quotient) ሆነ ከዐይን ዕይታ መድከም ጋር የሚገናኝ ዕክል አይደለም፡፡ ዲስሌክሲያ ያለባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ አማካይ ወይም ከአማካይ በላይ የአእምሮ ምጥቀት ያላቸው ናቸው።

ዲስሌክሲያን አስመልክቶ በመምህራን፣ ተማሪዎች እና ወላጆች ዘንድ ግንዛቤ ባለመኖሩ ወይም በጣም አናሳ በመሆኑ ዲስሌክሲያ ያለባቸው ተማሪዎች እንደ ሰነፍ እና ረባሽ ተማሪ ይቆጠራሉ። አስፈላጊውን እገዛ ባለማግኘታቸውና ቁጣና ነቀፋ ስለሚደርስባቸው በዕድሜ ከፍ እያሉ ሲሄዱ ትምህርታቸውን ያቋርጣሉ።

በዓለማችን ከ10 ሰዎች አንዱ ዲስሌክሲያ እንዳለበት ይገመታል። እንደ ዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ ከ17.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አካል ጉዳተኞች እንደሆኑ ይታሰባል። ይህ መረጃ የአካል ጉዳት ዐይነትን ለይቶ (Disaggregated Data) የሚያመላክት ባለመሆኑ ዲስሌክሲያ ያለባቸው ሰዎች መካተታቸውን ለማወቅ አያስችልም።

ዲስሌክሲያ ያለባቸው ሰዎች የመማር እና እኩል ዕድል የማግኘት መብቶች ያሏቸው ቢሆንም አብዛኛዎቹ ሰብአዊ መብቶቻቸውን ለመጠቀም ትልቅ እንቅፋት ይገጥማቸዋል። ባለፉት 30 ዓመታት የትምህርት ተደራሽነት ላይ የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም ከትምህርት ተሳትፎ ማነስ ጋር በተያያዘ 57 ሚሊዮን የሚደርሱ ሕፃናት ከትምህርት ቤት ውጪ እንደሆኑ እ.ኤ.አ. የ2015 የተባባሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በመጥቀስ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ያስቀምጣል[2]፡፡

ዲስሌክሲያን የመመርመሪያ መመዘኛዎች በአጠቃላይ በእንግሊዘኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ይህ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንግሊዘኛ ላልሆነ ሰዎች ምርመራ ለማድረግ ትልቅ ክፍተትን ያስከትላል፡፡[3] በመሆኑም ኢትዮጵያ እንግሊዘኛ ሦስተኛ ወይም አራተኛ ቋንቋ ተናጋሪ እንደመሆኗ ለእንግሊዘኛ ተናጋሪ ሕጻናት የተነደፉት የዲስሌክሲያ ምርመራ መመዘኛዎች ለኢትዮጵያዊ ልጅ ትክክለኛ የምርመራ ውጤት አያሳዩም፡፡ የተለያዩ ማኅበረ-ባህላዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ የምርመራ መመዘኛዎች አለመዘጋጀታቸው ዲስሌክሲያ ያለባቸውን ሰዎች ለመለየትና ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ አዳጋች አድርጎታል።

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነትን በአዋጅ ቁጥር 676/2002 አጽድቃ የሀገሪቱ ሕግ አካል አድርጋለች። በዚህ ስምምነት መሠረት ተዋዋይ መንግሥታት አካል ጉዳተኞች ላላቸው የመማር መብት ዕውቅና እንዲሰጡና መብቱ ያለአድልዎ፣ በእኩል ዕድል ላይ ተመሥርቶ በሥራ ላይ እንዲውል ለማስቻል በሁሉም ደረጃዎች የአካትቶ-ትምህርት ሥርዓትን ተፈጻሚነት እንዲያረጋግጡ ይገደዳሉ። በመሆኑም ኢትዮጵያ ዲስሌክሲያ ላለባቸው ሰዎች እኩል ዕድሎችንና የትምህርት፣ የጤና አጠባበቅ፣ የሥራ ስምሪት እና የማኅበራዊ ተሳትፎ መብቶችን የማረጋገጥ ግዴታ አለባት።

እ.ኤ.አ. በ2025 የሚጠናቀቀው የኢትዮጵያ የልዩ ፍላጎት (አካቶ) ትምህርት መሪ ዕቅድ “በኢትዮጵያ ድህነት፣ ጾታ፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ የመማር እክል ሳይገድበው ለሁሉም ተማሪዎች ክፍት የሆነ የትምህርት ሥርዓት ተደራሽ ማድረግ” ራዕዩ መሆኑን ገልጿል። የዚህ መሪ ዕቅድ መርሕ ሁሉም ልጆች እና ተማሪዎች የተካተቱበት ፍትሐዊ የትምህርት ሥርዓት መዘርጋት እንደመሆኑ መንግሥት ይህንኑ ለማስተግበር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል።

ዲስሌክሲያ ያለባቸው ሰዎች ሙሉ ዐቅማቸውን በመጠቀም ለራሳቸው እና ለሀገራቸው ትርጉም ያለው አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ለማስቻል በማኅበረሰብ ውስጥ በሁሉም ዘርፍ የሚኖራቸውን የተሳትፎ መጠንና የአገልግሎት ተደራሽነት ማሳደግ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም ሰብአዊ መብቶቻቸው ሙሉና ውጤታማ በሆነ ደረጃ እንዲረጋገጡ ማድረግ ይገባል። ይህንን ለማሳካት ዲስሌክሲያ አንዱ የብዝኃነት መገለጫ መሆኑን በመገንዘብ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።

ስለሆነም ከዘላቂ ልማት ግቦች መካከል ጥራቱን የጠበቀና አካታች ትምህርት ተረጋገጠ የሚባለው በ2023 ዓ.ም. አካታች እና ሁሉም የትምህርት ዕርከኖች ለሕፃናትና ለሌሎች አካል ጉዳተኞች ተደራሽ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው። መንግሥት ይህንን ከግምት በማስገባት ዲስሌክሲያ ያለባቸውን ሰዎች ልዩ ፍላጎት ያማከለ የትምህርት ሥርዓት መዘርጋት፣ መምህራን እና ወላጆች/አሳዳጊዎች በዲስሌክሲያ ዙሪያ ያላቸውን ዕውቀት ማጎልበት፣ ለኢትዮጵያዊ ልጆች የሚመጥን የዲስሌክሲያ መመርመሪያ መመዘኛ ማዘጋጀት፣ በተመጣጣኝ ዋጋ የምርመራ አገልግሎቶችን እና አስፈላጊውን ሕክምና የሚሰጡ ማእከሎችን ማቋቋም እንዲሁም ዲስሌክሲክ ለሆኑ ሕፃናት በትምህርት ቤት ውስጥ አስፈላጊው ተመጣጣኝ ማመቻቸት ማድረግ ይጠበቅበታል።


[1]Lexercise: https://shorturl.at/nGOS7

[2] Inclusive education: Children with disabilities: https://shorturl.at/ilFV4; See also Save the Children: https://shorturl.at/hkwDO

[3] https://shorturl.at/alpq1.