የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከግንቦት ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ወቅቶች በተከሰቱ ግጭቶች እና የጸጥታ መደፍረስ ሁኔታዎች ሳቢያ የደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ የተደረገ የምርመራ ሪፖርት የካቲት 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ኮሚሽኑ በምርመራ ሪፖርቱ በተለዩ ግኝቶችና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሚያዝያ 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በጋምቤላ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የኮሚሽኑ፣ የፌዴራል መንግሥት እና የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በውይይቱ ኮሚሽኑ በጋምቤላ ክልል በጎግ ወረዳ፣ በጋምቤላ ወረዳ፣ በኢታንግ ልዩ ወረዳ አቹዋ ቀበሌ፣ ፒኖ ንዑስ ቀበሌ፣ እንዲሁም ቴምፒኝ መንደር እና በጋምቤላ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶችና ጥቃቶች የተነሳ በተፈጸሙ ግድያዎች፤ በደረሱ የአካል ጉዳቶች፤ የንብረት ውድመቶች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ባከናወነው ምርመራ የተለዩ ግኝቶችና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ለተሳታፊዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። እንዲሁም በክልሉ በሚገኙ ስደተኞች እና ተቀባይ ማኅበረሰብ ላይ የደረሱ ጉዳቶች በውይይቱ የቀረቡ ሲሆን መሰል ችግሮች በቀጣይ እንዳይከሰቱ በሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መከናወን በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር ተደርጓል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ኮሚሽኑ በክልሉ ተከስተው በነበሩ ግጭቶችና በተፈጸሙ ጥቃቶች ላይ ባከናወነው ምርመራ የለያቸው ግኝቶችና ያቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች የችግሮቹን ስፋትና ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በክልሉ በተደጋጋሚ የሚከሰቱ ግጭቶች መንስኤዎች ላይ ኮሚሽኑ ተጨማሪ ጥናት እና ምርመራዎችን እንዲያደረግ እንዲሁም የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች እንዲፈጸሙ በቅርበት እንዲከታተል ጠይቀዋል።

በውይይቱ ኮሚሽኑ የምርመራ ሪፖርቱን ይፋ ካደረገ በኋላ በክልሉ መንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ተገቢ እና አበረታች መሆናቸውን የገለጸ ሲሆን በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶችና ጥቃቶች አሁንም በመቀጠላቸው በክልሉ የሚገኙ የጸጥታ መዋቅሮችን በመፈተሽ ብቁ፣ ሚዛናዊ እና ግጭቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋጋት የሚያስችላቸውን ዐቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል። በተጨማሪም በስደተኞች እና በተቀባይ ማኅበረሰብ መካከል ያሉ አለመግባባቶች እና ያለመግባባት ምክንያቶች በዘላቂነት የሚፈቱበትን መንገድ ለመፍጠር የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጥረቶችን ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁሟል።