የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ሃዋሳ፣ ሻሸመኔ እና ወላይታ ከተሞች በሚገኙ 21 የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ባከናወነው የምክረ ሐሳቦች አፈጻጸም ክትትል ግኝቶች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል። በውይይቱ የሐረሪ፣ የኦሮሚያ፣ የሲዳማ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የሴቶች፣ የሕፃናት እና የማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ኃላፊዎች እንዲሁም የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ኢሰመኮ በማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ ከሚገኙ ሕፃናት መብቶች አያያዝ ጋር በተያያዘ ያከናወነው ክትትል ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎችን መሠረት ያደረገ ሲሆን፤ በተለይም የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት የቅበላ መሥፈርቶች እና መረጃ አያያዝ፣ የሕፃናት ከጥቃት የመጠበቅ መብት፣ የቅጣት (የዲሲፕሊን) እርምጃዎች፣ የጤና፣ የሥነ ልቦና፣ የትምህርት፣ የጨዋታ እና የመዝናኛ አገልግሎቶች፣ የእምነት ነጻነት እና የተሳትፎ መብቶችን በተመለከተ የተለዩ ግኝቶች፣ አሳሳቢ ሁኔታዎች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።


የውይይቱ ተሳታፊዎች በኢሰመኮ ተለይተው የቀረቡ ግኝቶች ክትትል በተደረገባቸው ተቋማት ውስጥ ያሉ ሕፃናት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን የሚያሳዩ እንደሆኑ እና የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችም በቀጣይ ለሚወሰዱ እርምጃዎች መሠረት መሆናቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም በተቋማቱ ለሚገኙ ሕፃናት ዘላቂና የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት፣ በተቋማት መካከል የተጀመሩ መልካም ግንኙነቶችን ለማጠናከር እና የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን መፍታት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መልካም ተሞክሮ ለመቅሰም የሚያግዝ ቅንጅታዊ አሠራር ሊዘረጋ እንደሚገባ ገልጸዋል። በውይይቱ ማጠናቀቂያ ተሳታፊዎች የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ለመፈጸም የሚረዱ በየተቋሞቻቸው የሚፈጸሙ ተግባራትን በመለየት በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚተገበሩ የምክረ ሐሳብ አፈጻጸም የድርጊት መርኃ ግብር አዘጋጅተዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች እና የሕፃናት መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ በማሳደጊያ ተቋማት ያሉ ሕፃናት ሰብአዊ መብቶችን ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶችና የተገኙ ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን በመግለጽ፤ የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት በድርጊት መርኃ ግብር ያቀዷቸውን በተለይም በአሳሳቢነት ለተለዩ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። አክለውም ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይ የሚያከናውነውን የድጋፍና የክትትል ሥራ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።