የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2014 ዓ.ም. በሶማሌ ክልል ከሚገኙ ማረሚያ ቤቶች መካከል በአራት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ላይ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ክትትል አከናውኗል። በክትትሉ ታራሚዎችን እና የማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎችን ቃለመጠይቅ በማድረግ፣ ውይይት እና አካላዊ ምልከታ በማከናወን ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ማሳየት የሚችል መረጃ የማሰባሰብ ሥራ ሠርቷል፡፡ ኢሰመኮ በክትትሉ በለያቸው ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. በጅግጅጋ ከተማ ውይይት አድርጓል፡፡
በውይይቱ ወቅት ከክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ ከተባባሩት መንግሥታት የአደገኛ መድኃኒት እና ወንጀል መከላከል ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያ ቢሮ፣ ከሴንተር ፎር ጀስቲስ፣ ከዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ እና ከክልሉ ምክር ቤት፣ የፍትሕ ቢሮ፣ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ የተወጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ከዚህ ቀደም የማእከላዊ ማረሚያ ቤት (ጄል ኦጋዴን) እና የጎዴ ማረሚያ ቤት በመባል የሚታወቁ ሁለት ማረሚያ ቤቶች ብቻ ነበሩት። ሀገራዊ የፖለቲካ ለውጥ መደረጉን ተከትሎ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ይፈጸምበት የነበረው ጄል ኦጋዴን በመዘጋቱ በክልሉ ያሉትን ታራሚዎች በአግባቡ ለማስተናገድ መንግሥት 6 ተጨማሪ ማረሚያ ቤቶች እንዲከፈቱ አድርጓል፡፡
ኢሰመኮ በክትትሉ በሸፈናቸው ማረሚያ ቤቶች በታራሚዎች እና በማረሚያ ቤቶች አስተዳደር መካከል ጥሩ ግንኙነት መኖሩ፣ ድብደባ እና መሰል ኢሰብአዊ ጥቃቶች አለመኖር፣ አሳሳቢ የሆነ የታራሚ መጨናነቅ የሌለ መሆኑ፣ ተጨማሪ ማስፋፊያ ለማድረግ እና ያሉትን ማረሚያ ቤቶች ደረጃቸውን ለማሳደግ ጥረቶች መጀመራቸው፣ ታራሚዎች የሃይማኖት ነጻነት እና የማምለኪያ ቦታዎች ያላቸው መሆኑ በጠንካራ ጎን ተለይተዋል፡፡
በሌላ በኩል በክልሉ የሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ለወጣት ጥፋተኞች እና ለሴቶች የተለየ በቂ የማቆያ ቦታ አለመኖሩ፣ ታራሚዎች በጥፋታቸው ደረጃ ተለያይተው የማይያዙ መሆኑ፣ በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች ያሉ ጤና ጣቢያዎች በቂ የመመርመሪያ መሣሪያ እና መድኃኒት አለመሟላት፣ የቀለም እና የሙያ ትምህርት ከመስጠት አንጻር ሰፊ ውስንነቶች ያሉባቸው መሆኑ እንዲሁም የመዝናኛ አገልግሎት አለመኖር ከተለዩ ክፍተቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ የጀረር እና የቀብሪደሃር ማረሚያ ቤቶች ከፖሊስ ጣቢያነት ወደ ማረሚያ ቤትነት የተለወጡ በመሆናቸው ሙሉ የማረሚያ ቤት አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ስላልሆኑ ማሻሻያ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ተጠቅሷል፡፡
የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች የክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ሪጅናል ዳይሬክተር ኢማድ አብዱልፈታህ፤ የክልሉ መንግሥት እና የክልል የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ከዚህ በፊት በማረሚያ ቤቶች ይታዩ የነበሩ ኢሰብአዊ አያያዞችን ለማስቀረት የወሰዷቸው እርምጃዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል። አክለውም በክትትሉ የተለዩ በተለይም ከበጀት ጋር የተያያዙ ክፍተቶችን በሂደት ለመቅረፍ እየጨመረ የሚሄድ በጀት በመመደብ የተሻለ የታራሚዎች አያያዝ እንዲኖር መንግሥት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም በማረሚያ ቤቶች ላይ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን እያደረገ ያለውን ጥረት እንዲደግፉ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡
የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር በሺር አህመድ ሃሺ በበኩላቸው ማረሚያ ቤቶቹን በሚፈለገው ልክ ለማሻሻል የበጀት እጥረት ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰው በኢሰመኮ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝት እንደሚሠሩ በማረጋገጥ በዚህ ረገድ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡