የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ 12 እስከ ሰኔ 16 ቀን 2013 ድረስ ምርጫ በተካሄደባቸው በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የተመረጡ አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ የክትትል ቡድን በማሰማራት ያጠናቀረውን የሰብአዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ፣ ክትትሉ በተከናወነባቸው የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎችና አካባቢዎች የተመለከታቸው ክፍተቶች ተገቢው ትኩረት እንዲያገኙና አስፈላጊውን የሕግና የአተገባበር መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገለጸ።

ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምርጫ 2013 ዓ.ም. ባለ6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ ይፋ በማድረግና ለሰብአዊ መብቶች ትኩረት እንዲሰጥ ከመወትወት በተጨማሪ፤ በቅድመ ምርጫውና በምርጫው ቀን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ሲያከናውን ቆይቷል። በተለይም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመዘዋወር፣ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶችን በተመለከተና የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ እንዲሁም ምርጫው የአካል ጉዳተኞችን እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ያሳተፈና ለእነሱ ተደራሽ የሆነ በማድረግ ረገድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።

በዚህም መሰረት 94 ባለሞያዎችን ያካተተው ቡድን በአጠቃላይ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ ከተሞችና በሁሉም ምርጫ በተካሄደባቸው ክልሎች በሚገኙ 99 የምርጫ ክልሎችና 404 የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውሮ፣ የአካባቢውን አስተዳደር፣ ነዋሪዎችን፣ የፀጥታ ኃይሎችን እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን፣ እጩዎችንና አባላት እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚ አካላትና ሌሎች ባለድርሻዎችን አነጋግሯል። በዋና ጽሕፈት ቤቱ በተመደቡ ባለሞያዎች አማካኝነት በ7037 የስልክ ቁጥሩ ጥቆማዎችንና አቤቱታዎችን ተቀብሎ አስተናግዷል።

ምርጫው የተካሄደበት አውድ በሀገር ውስጥ የተደራረቡ ችግሮች የገጠሙበት እና በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ባሉበት፣ በተወሰኑ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምርጫው እንዲተላለፍ አስገዳጅ በሆነበት፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖች እራሳቸውን ከምርጫው ሂደት ባገለሉበት፣ ሌሎች የፖለቲካ ቡድን አመራሮች በቀረበባቸው የወንጀል ክስ ምክንያት በእስር በሚገኙበት ወቅት መሆኑ የማይዘነጋ መሆኑንና ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ኮሚሽኑ ገልጿል። ይህ ተግዳሮት እንዳለ ሆኖ፤ ኢሰመኮ በምርጫው መዳረሻ ቀናት እና በምርጫው እለት ክትትል ባደረገባቸው አካባቢዎች የተወሰኑ የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ክፍተት የታየ ቢሆንም፤ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች የጎላ ወይም የተስፋፋ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳልታየ ገልጾ፤ ክትትል ባደረገባቸው በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች የምርጫው ዕለት ሂደት ያለ የጎላ ችግር በሰላም ተጀምሮ የተጠናቀቀና በሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ረገድ በብዙ መልኩ የተሳካ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እንደነበር አሳውቋል። በተጨማሪም በምርጫው ሂደት በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለተሳተፉና አስተዋጾ ላደረጉ ወገኖች ሁሉ እውቅና ሰጥቶ፤ በቀሪው ሂደትም በሕጋዊና ሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መንገድ እንዲቀጥሉ ጥሪውን በድጋሚ አቅርቧል።

እነዚህን አወንታዊና አበረታች እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ከምርጫው እለት ጥቂት ቀናት በፊት፣ በምርጫው እለትና ከምርጫው ቀን በኋላ የደረሰ የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት፣ ተገቢ ያልሆነ እስር፣ በመራጮች ላይ የደረሰ ማስፈራራት፣ በምርጫ ታዛቢዎችና ጋዜጠኞች ላይ ስለደረሰ መጉላላትና ማዋከብ፣ የምርጫው ሂደት ለአካል ጉዳተኛ ሰዎች ያለው ተደራሽነትና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የተሳትፎ መጠን በሚመለከት ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት አስረድቶ፤ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል።

በተጨማሪም ጥፋተኛ በሆኑ ሰዎች ላይ በአፋጣኝ ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነታቸው እንዲረጋገጥ እና ኮሚሽኑ በሕግ የተሰጠውን በምርጫ ወቅት የሰብአዊ መብቶች ክትትል የማድረግ ኃላፊነቱንና ተግባሩን በአግባቡ እንዳይወጣ የሚያግዱ፣ የሚገድቡ ወይም የሚያሰናክሉ ሁኔታዎች በተለይም የምርጫ ጣቢዎችን ያለ እንቅፋት የመጎብኘት አስፈላጊነት እና የእስር ቦታዎችን ያለ ቅድሚያ ማስታወቂያ የመጎብኘት አስፈላጊነት በሚመለከት ለወደፊቱ ማናቸውም አይነት እንቅፋት እንዳይከሰት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካሎች ሁሉ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱና ሁሉም ሰዎችና ተቋሞች ለኮሚሽኑ ስራ የመተባበር ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስቧል።

https://ehrc.org/am/download/%e1%89%a02013-%e1%8b%93-%e1%88%9d-%e1%88%80%e1%8c%88%e1%88%ab%e1%8b%8a-%e1%88%9d%e1%88%ad%e1%8c%ab-%e1%8b%b5%e1%88%9d%e1%8c%bd-%e1%88%98%e1%88%b5%e1%8c%ab-%e1%89%80%e1%8a%95-%e1%8b%a8%e1%89%b0/