የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ 2013 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ባለ 37 ገጽ ዓመታዊ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል፡፡
ይህ ዓመታዊ የዘርፍ ሪፖርት ኢሰመኮ በሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት ላይ በተጨማሪነት በተለይ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ በዝርዝር በማተኮር ባለፈው የበጀት ዓመት ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ልዩ ልዩ ተግባራት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች አያያዝን በተመለከተ የለያቸውን መልካም ጅማሮዎች፣ አሳሳቢ ሁኔታዎችንና ተግዳሮቶችን እንዲሁም በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሊተገበሩ የሚገባቸውን ምክረ ሃሳቦች አካቷል፡፡
ኢሰመኮ በተለይ ኃይል በተሞላበት ግጭት እና ሌሎች ሰው ሠራሽ መንሥኤዎች በከፍተኛ ቁጥር ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ፣ ከተቀባይ ማኅበረሰብ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ፣ በተለያዩ ቦታዎች እንዲሰፍሩ የተደረጉ እንዲሁም ወደ ቀድሞ የመኖሪያ አካባቢያቸው የተመለሱ ተፈናቃይ ተመላሾችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አስመልክቶ ከሰኔ 2013 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም. ባሉት 12 ወራት ውስጥ ያከናወናቸውን የክትትል እና ምርመራ ሥራዎች መሰረት በማድረግ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሲከታተል ቆይቷል፡፡ ይህ ዓመታዊ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት የእነዚህ ክትትሎች ውጤት ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን አስመልክቶ የተገኙ ቁልፍ እመርታዎች፣ ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች እና ምክረ-ሃሳቦች አካቷል፡፡ በሪፖርቱ የተጠቀሱ አንዳንድ ክስተቶችና ሁነቶች በመጠነ ሰፊነታቸው አልያም በዓይነታቸው አማካኝነት የሪፖርቱን ምክረ-ሃሳቦች በይበልጥ ለማጠናከር እንዲሁም አካባቢያዊ አውዶችን በተሻለ ሁኔታ ለመግለጽ እንዲረዱ የተመረጡ ናቸው።
ኮሚሽኑ የክትትል እና ምርመራ ሥራዎቹን ያከናወነው አግባብነት ያላቸውን የሰብአዊ መብቶች መስፈርቶች በመጠቀም በተዘጋጁ መለኪያዎች/መስፈርቶች፣ መጠይቆችና መመሪያዎች ላይ በመመስረት ነው፡፡ በዓመታዊ ሪፖርቱ ውስጥ የተካተቱት መረጃዎች እና ማስረጃዎች፤ ኮሚሽኑ ባደረገው የክትትል እና ምርመራ ሥራ ግኝቶች፣ በግለሰቦች በቀረቡ አቤቱታዎች፣ በመለስተኛ ጥናቶች እና የምክክር መድረክ ግብአቶች ላይ የተመረኮዙ ናቸው።
ሪፖርቱ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ምዝገባ እና ሰነድን የማግኘት መብት፣ የፀጥታና ደኅንነት እንዲሁም የመንቀሳቀስ መብት፣ የሰብአዊ ድጋፍ የማግኘት መብት፣ ለሕፃናት፣ ሴቶች፣ አረጋውያን እና አካል ጉዳተኛ ተፈናቃዮች የሚደረግ ልዩ ድጋፍ እንዲሁም በአጠቃላይ የዘላቂ መፍትሔዎች አተገባበር ላይ ትኩረት በማድረግ በ6 ክልሎች እና በአንድ ከተማ አስተዳደር 1.5 ሚሊዮን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሚያስጠልሉ 52 መጠለያዎችን፣ ጣቢያዎችን እና ተቀባይ ማኅበረሰቦች ላይ የተሠሩ የክትትል እና የምርመራ ሥራዎች ግኝቶች እና ምክረ-ሃሳቦች አካቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 6ኛውን ብሔራዊ ምርጫ እና የተፈናቃዮች ተሳትፎን አስመልክቶም ኮሚሽኑ የሠራውን የዳሰሳ ጥናት ግኝቶች አካቷል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ ስምምነትን (የካምፓላ ስምምነት) ካጸደቁ 33 የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ስትሆን ስምምነቱ ብሔራዊ ሕግ እና ተቋማዊ መዋቅር እንዲኖር ማስቻልን ዋነኛ የመንግሥት ኃላፊነት በማድረግ በደነገገው መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት የስምምነቱን ማስፈጸሚያ ሕግ ለመቅረጽ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ሪፖርቱ እንደ አንድ ቁልፍ እመርታ አካቷል።
ከዚህ በተጨማሪ ምንም እንኳን ተግዳሮቶች ቢኖሩትም፤ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ልዩ ሁኔታ የሚቋቋሙ የምርጫ ጣቢያዎች መመሪያ ቁጥር 13/2013 በመጽደቁ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በ6ኛው ብሔራዊ ምርጫ በመራጭነት እንዲሳተፉ ማስቻሉ እንደመልካም እርምጃ ጠቅሷል። የሶማሌ ክልል እ.ኤ.አ. ከ2022 – 2025 በሥራ ላይ የሚውል የዘላቂ መፍትሔ ስትራቴጂ ሰነድ መቅረጹ በክልል ደረጃ ለተፈናቃዮች የዘላቂ መፍትሔ ለማመቻቸት ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር በመሆኑ የተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከማሻሻል አንጻር እንደመልካም ተሞክሮ በሪፖርቱ ተካቷል።
ሆኖም ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጥበቃ እና ድጋፍ የካምፓላ ስምምነትን ካጸደቀች በኋላ ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ አለመዘጋጀቱና ተቋማዊ አደረጃጀት አለመኖሩ፤ መፈናቀልን የመከላከል፣ ለተፈናቃዮች የሚደረጉ የጥበቃ እና ድጋፍ ሥራዎች እንዲሁም የዘላቂ መፍትሔ የማመቻቸት ሂደቱን ማስተጓጎሉ በሪፖርቱ ከተጠቀሱ ክፍተቶች መካከል አንዱ ነው።
የተፈናቃዮች ምዝገባና ሰነድ የማግኘት ሥርዓት ላይ የተስተዋሉ ችግሮችም ግልጽ የሕግ ማዕቀፍና ተቋማዊ አደረጃጀት ካለመኖር የሚመነጩ በመሆናቸው እና ከዚህ ጋር ተያይዞ የተስተዋሉ ክፍተቶች ለተፈናቃዮች የሚደረገው ድጋፍ በአግባቡ እንዳይከናወን አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድረዋል።
ወቅቱን የጠበቀ፣ በቂ፣ ተደራሽ እንዲሁም ልዩ ጥበቃ እና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው እንደ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ያሉ ተፈናቃዮችን ልዩ ፍላጎቶች መሰረት ያደረገ የሰብአዊ ድጋፍ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ ክፍተት መኖሩን፣ በዚህም ምክንያት የተፈናቃዮች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ ሴቶች እና ሕፃናት ተፈናቃዮች ተፈናቅለው ባሉበት አካባቢ ለጥቃት ተጋላጭ በሚያደርጋቸው ሁኔታ ውስጥ ያሉ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
የዘላቂ መፍትሔ አማራጮች አተገባበርም የመፈናቀል መንሥኤ የሆኑትን የፀጥታ እና ደኅንነት ሥጋቶች ባስወገደ መልኩ አለመሆኑ፣ ተፈናቃዮችን እና ተቀባይ ማኅበረሰብን ባሳተፈ፣ የተፈናቃዮችን ፍላጎት ባገናዘበ፣ እንዲሁም ተፈናቃዮችን በዘላቂነት በሚያቋቁም ሁኔታ ባለመሆኑ ተፈናቃዮችን ለዳግም መፈናቀል እና ለተራዘመ መፈናቀል መዳረጉ በሪፖርቱ ከተዘረዘሩት ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ የካምፓላ ስምምነት አባል ሀገር እንደመሆኗ፤ በስምምነቱ ውስጥ የተካተቱ የሰነድና ምዝገባ፣ የፀጥታና ደኅንነት፣ የመንቀሳቀስ ነፃነት እና ፍትሕ የማግኘት መብት፣ የሰብአዊ ድጋፍና መሰረታዊ አገልግሎቶችን የማግኘት መብት፣ የዘላቂ መፍትሔዎችን አተገባበር እንዲሁም ልዩ ጥበቃ የማግኘት መብቶችን እና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የመብቶች አጠባበቅ የተጣሉ ግዴታዎች ዙሪያ የተስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ማሻሻል እንደሚገባ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አሳስቧል።
የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ሰብአዊ መብቶች ለማሻሻል ኮሚሽኑ ባዘጋጃቸው ምክክሮች ግብዓት በመስጠትና ምክረ-ሃሳቦችን በመተግበር ኃላፊነታቸውን ለተወጡ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ምስጋናቸው አቅርበው፤ በአሁኑ ወቅት ግን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ተገቢውን ፈጣን ምላሽ እያገኘ ባለመሆኑ የሰብአዊ መብቶቻቸው አያያዝ ሁኔታ የከፋ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ተፈናቃዮችም ለተራዘመ የመፈናቀል ሁኔታ እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ሰብአዊ መብቶች መጠበቅና ሁኔታቸውን ማሻሻል ብሔራዊ ቁርጠኝነት የሚሻ እና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ እና ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን የመፈናቀል ሰለባ ሲሆኑ ደግሞ ለተደራራቢ የመብት ጥሰት ስለሚዳረጉ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አክለው ገልጸዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም “መንግሥት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ሰብአዊ መብቶች በአግባቡ ለመጠበቅ ቁልፍ መፍትሔ የሆነውን እና በአሁኑ ወቅት በሂደት ላይ ያለውን የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት በማጠናከር የተፈናቃዮችን ሰብአዊ መብቶች በበቂ ሁኔታ የሚያስጠብቅ ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት ይገባል። የተፈናቃዮችን ጥበቃ እና ድጋፍ የሚያስተባብር ተቋማዊ መዋቅር እንዲዘረጋ፣ እንዲሁም የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ለተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች መከበር የበኩላቸውን እንዲወጡ በሪፖርቱ የተጠቀሱ ምክረ-ሃሳቦችን እንዲያስፈጽሙ በድጋሚ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል።
Annual Report on the Human Rights Situation of Internally Displaced Persons in Ethiopia