ትርጓሜ
ማሠቃየት እና ሌሎች ጭካኔ የተሞላባቸው ኢ-ሰብአዊና አዋራጅ አያያዞችንና ቅጣቶችን ለማስቀረት በተደረገ ስምምነት (የፀረ-ማሠቃየት ስምምነት) መሠረት የማሠቃየት ወንጀል የሚከተሉትን ሦስት ዋና ዋና ሁኔታዎች በውስጡ የያዘ ነው፦
- ከፍተኛ ሕመም ወይም ሥቃይ የሚያስከትል መሆኑ፤
- ከፍተኛ ሕመም ወይም ሥቃይ የሚያስከትለው ተግባር የተፈጸመው መረጃን ለማግኘት ወይም ለማናዘዝ እና የእምነት ቃል ለመቀበል ለማሸማቀቅ ዓላማ መዋሉ፤
- ድርጊቱ የተፈጸመው በመንግሥት ባለሥልጣን ወይም በሌላ የመንግሥት ሥልጣን ይዞ በሚሠራ ሰው ወይም በእሱ/ሷ አነሳሽነት፣ ፍቃድ ወይም ተቀባይነት መሆኑ።
የማሠቃየት ተግባር ምን ተጽዕኖዎችን ያስከትላል?
የማሠቃየት ድርጊት ተጽዕኖዎች አካላዊ ወይም ሥነ-ልቦናዊ ሊሆኑ ይችላሉ።
አካላዊ:– የማሠቃየት ድርጊት የረጅም ጊዜ አካላዊ ጉዳት እና ተጽዕኖዎች ጠባሳ፣ ራስ ምታት፣ የጡንቻ ሕመም፣ የእግር ሕመም፣ የመስማት ችሎታን ማጣት፣ የልብ ወይም የመተንፈስ ችግር፣ እና ሌሎች የነርቭ ጉዳትን ያካተተ ሊሆን ይችላል።
ሥነ-ልቦናዊ:- የማሠቃየት ድርጊትን ተከትሎ ከሚመጡ ሥነ-ልቦናዊ ችግሮች እንቅልፍ ማጣት፣ የማስታወስ ችሎታ ማጣት፣ ድካም፣ ጭንቀት፣ ድብርት፣ ከአሰቃቂ ድርጊት በኋላ የሚፈጠር ጭንቀት እና ትኩረት የማጣት ችግርን ያጠቃልላሉ።
የማሠቃየትን ተግባርን የሚከለክሉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የትኞቹ ናቸው?
ከዓለም አቀፉ የማሠቃየት ድርጊትን ለመከላከል ስምምነት በተጨማሪ ሁሉም ዋና ዋና የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች፣ እንዲሁም የሲቪል እና ፖለቲካዊ መብቶች ቃልኪዳን ጨምሮ የማሠቃየት ድርጊቶችን ፍጹም ይከለክላሉ። ማንኛውም ዓይነት የማሠቃየት ተግባር ሊተገበር የሚችልበት ልዩ ሁኔታ የለም።
የማሠቃየት ተግባር በማንኛውም ልዩ ሁኔታ፤ በጦርነት ወይም የጦርነት ሥጋት፤ በውስጥ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ወይም በሌላ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎች ሕጋዊ መከላከያ ሊሆን አይችልም። ይህ ክልከላ ሀገራት የማሠቃየት ተግባርን በግልጽ የሚከለክሉ ስምምነቶችን ባያጸድቁም በሁሉም ሀገራት ላይ አስገዳጅ የሆነ የልማዳዊ ዓለም አቀፍ ሕግ አካል ነው።
ሆኖም የማሠቃየት ተግባር የፈጸመ ሰው ድርጊቱን የፈጸመው ከበላይ አካል በተላለፈ ትእዛዝ መሆኑን ገልጾ ከወንጀል ቅጣት ነጻ መሆን አይችልም።
ከበላይ አካል ወይም ከመንግሥት ባለሥልጣን የሚተላለፍ ትእዛዝ ለማሠቃየት ተግባር ሕጋዊ መከላከያ ሊሆን አይችልም።
የማሠቃየት ተግባር በሕግ የተቀመጠ ይርጋ የለውም። በዚህ ወንጀል የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው በማንኛውም ጊዜ ክስ ሊቀርብበት ይችላል።
የስምምነቱ አባል ሀገራት የሚከተሉት ኅላፊነት አለባቸው:-
- ሀገራት የማሠቃየት ተግባርን በሕግ፤ በአስተዳደር፤ በፍርድ ሥርዓት እና ሌሎች እርምጃዎችን የመከላከል፤
- የማሠቃየት ተግባር ወንጀል መሆኑን ሀገራት በወንጀል ሕጋቸው ማስቀመጥ አለባቸው፤
- የማሠቃየት ተግባር ተፈጽሟል ብሎ ለማመን የሚያስችል ምክንያት ሲፈጠር ሀገራት ፈጣን እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲሁም ተጎጂው ካሳ እንዲያገኝ ሊያደርጉ ይገባል።
የማሠቃየት ተግባራትን የሚከለክሉ የኢትዮጵያ ሕጎች የትኞቹ ናቸው?
የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 18 ሁሉም ሰው ከማሠቃየት እና ሌሎች ጭካኔ የተሞላባቸው፤ ኢ-ሰብአዊና አዋራጅ አያያዝ እና ቅጣቶችን የመጠበቅ መብት እንዳለው በግልጽ ያስቀምጣል። የሕግ-መንግሥቱ ድንጋጌ ምንም ዓይነት ልዩ ሁኔታዎችን ባለማስቀመጡ ይህ መብት ማናቸውም ሁኔታ ሊጣስ እንደማይገባ ያረጋግጣል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ወንጀል ሕግ፤ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 720/2004 (በአዋጅ ቁጥር 944/2008 እንደተሻሻለው) እና የፌዴራል ማረሚያ ቤት አዋጅ ቁጥር 1174/2012 የታራሚዎችን እና የታሰሩ ሰዎችን መብት እና ደኅንነት ከማሠቃየት እና ኢ-ሰብአዊ አያያዞች እና ቅጣት የመጠበቅ መብትን ጨምሮ ሌሎች ድንጋጌዎችን ያካትታሉ።
ሆኖም የወንጀል ሕጉም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ሕጎች በፀረ-ማሠቃየት ስምምነቱ አንቀጽ 1 ላይ በተቀመጠው መሠረት “ማሠቃየት’’ ለሚለው ቃል የተሟላ ትርጓሜ ባያስቀምጡም ኢትዮጵያ በ1986 ዓ.ም. የፀረ-ማሠቃየት ስምምነቱን ያጸደቀች በመሆኑ በሰነዱ ላይ የማሠቃየት ተግባራት ትርጓሜ በሙሉ ተፈጻሚ ይሆናል።
የማሠቃየት ተግባር ሰለባ ለሆኑ ተጎጂዎች በዓለም አቀፍ ሕጎች የተቀመጠ ምን መፍትሔዎች አሉ?
የማሠቃየት ተግባር ሰለባ ለሆኑ ተጎጂዎች ፍትሐዊና በቂ ካሳ አግኝተው በተቻለ መጠን ከጉዳቱ ሙሉ በሙሉ የሚያገግሙበት ሁኔታ የሚፈጥር የሕግ ሥርዓት መዘርጋት አለበት።
የአፍሪካ የሰዎች እና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽን ካሳን በተመለከተ ባወጣው አጠቅላይ ትንታኔ ተጎጂዎች ሊሰጣቸው ስለሚገባ መፍትሔ እና ካሳ እንደሚከተለው ይዘረዝራል፡-
- የማሠቃየት ተግባር ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎች ሊለካ የሚችል ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችን የሚተካ ፍትሐዊ እና በቂ ካሳ የማግኘት መብት እንዳላቸው፣
- የማሠቃየት ተግባር ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎች ከጉዳቱ በፊት የነበሯቸው ወይም አዲስ ችሎታዎች እንዲኖራቸው እና ወደነበሩበት ማኅበረሰብ ሙሉ በሙሉ እንዲመለሱ እና እንዲሳተፉ የአካል፤ የአእምሮ፤ የባህል እንዲሁም የመንፈስ ነጻነት የመመለስ መብት እንዳላቸው፣
- ተጎጂዎችን የማሠቃየት ተግባሩ ከመፈጸሙ በፊት ወደነበሩበት ሁኔታ እንዲመለሱ ማስቻል፣ እንዲሁም
- ሀገራት የማሠቃየት ተግባር ሲፈጸም በአፋጣኝ ገለልተኛ የምርመራ ሥራ ማካሄድ ይኖርባቸዋል፤ ተጎጂዎችም እውነቱን የማወቅ መብት እንዳላቸው።
የማሠቃየት ተግባር ሰለባ የሆነው ሰው በተፈጸመበት ተግባር ምክንያት በሚሞትበት ጊዜ በርሱ ኅላፊነትና ዕርዳታ ሥር ይተዳደሩ የነበሩ ሰዎች ካሳ እና የተሟላ መፍትሔ የማግኘት መብት አላቸው።