ሁለተኛ ደረጃ ጥቃት ምንድነው?
የጥቃት ተጎጂዎች ለደረሰባቸው አካላዊ፣ ጾታዊ፣ ወሲባዊ ወዘተ. ጥቃት የሕግ፣ የጤና፣ የማኅበራዊና ሥነ-ልቦናዊ ድጋፍ እና መፍትሔ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት በማኅበረሰቡ፣ በአገልግሎት ሰጪ ሰዎች ወይም በተቋማት ተጨማሪ ጉዳትና ጥቃት ሲደርስባቸው ሁለተኛ ደረጃ ጥቃት (Secondary Victimization) ወይም ድርብ ጥቃት (Double victimization) ወይም ድኅረ-ወንጀል ጥቃት (Post crime victimization) ይባላል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ጥቃት በመጀመሪያ ደረጃ ጥቃት አማካኝነት የደረሰውን ጉዳት የሚያባብስ ሲሆን፣ በተጎጂዎች የማገገም፣ መልሶ የመቋቋም፣ ፍትሕ እና ውጤታማ መፍትሔ የማግኘት እንዲሁም የመዳን ዐቅም ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ አለው፡፡
ሁለተኛ ደረጃ ጥቃት ከመጀመሪያ ደረጃ ጥቃት በምን ይለያል?
የመጀመሪያ ደረጃ ጥቃት እና የሁለተኛ ደረጃ ጥቃት ልዩነት በጥቃቱ ዐይነት፣ በጥቃቱ ምንጭ እንዲሁም ጥቃቱ በሚደርስበት ጊዜ ተከፋፍሎ ሊታይ ይችላል። የመጀመሪያ ደረጃ ጥቃት በተጎጂ ላይ ከተፈጸመው የወንጀል ድርጊት በቀጥታ የሚመነጩ አካላዊ፣ ወሲባዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ስሜታዊ እና የመሳሰሉትን ጥቃቶች ያጠቃልላል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ጥቃት ከመጀመሪያ ደረጃው ጥቃት ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ በወንጀል ድርጊቱ ቀጥተኛ ውጤት ሳይሆን ሰዎች እና ተቋማት ምላሽ በሚሰጡበት ጊዜ በተጎጂ ላይ የሚያደርሱትን ተጨማሪ ሥቃይና እንግልት የሚያመለክት ነው። ሆኖም፣ ከመጀመሪያ ደረጃ ጥቃት ጋር ተያያዥነት ያለው በመሆኑ ራሱን ችሎ ከሚፈጸም አዲስ እና የተለየ ጥቃት (new and separate incident) ይለያል።
በመጀመሪያ ደረጃ ጥቃት የጉዳቱ ምንጭ በተጎጂ ላይ የወንጀል ድርጊቱን ወይም ጥቃቱን የፈጸመው ሰው ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃ ጥቃት ግን በተጎጂ ቤተሰቦች፣ ጓደኞች፣ የሙያ ባልደረቦችና በአካባቢው ማኅበረሰብ ወይም ለጉዳት ምላሽ ለመስጠት በተቋቋሙ የፍትሕ እና የጤና ተቋማት ወይም ባለሞያዎች ወይም የተጎጂን ጉዳት፣ ክብርና ፍላጎት ያላገናዘበ ዘገባ በሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኃን ሊፈጸም ይችላል። ከጊዜ አንጻር፣ የመጀመሪያ ደረጃ ጥቃት የወንጀል ድርጊቱ ወይም ቀዳሚው ጥቃት በደረሰበት ጊዜና ቅጽበት የሚከሰት ሲሆን፣ ሁለተኛ ደረጃ ጥቃት ግን የመጀመሪያው ጥቃት ከደረሰ በኋላ ለምሳሌ ተጎጂዎች የደረሰባቸውን ጉዳት ለቅርብ ቤተሰብ ወይም ጓደኛ በሚያስረዱበት ጊዜ ወይም በፍትሕ አስተዳደር ሂደት ውስጥ በአቤቱታ አቀራረብ፣ በምርመራ፣ በክስ አቀራረብና አሰማም እንዲሁም በድኅረ ችሎት ሂደቶች፣ በተቀናጀ የአንድ ማእከል አገልግሎት መስጫ ማእከላት ወይም በመጠለያ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ በሚያልፉበት ጊዜ ሊከሰት የሚችል ነው፡፡
በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርስ ሁለተኛ ደረጃ ጥቃት መገለጫዎች ምንድን ናቸው?
ማንኛውም የጥቃት ተጎጂ የሆነ ሰው ሁለተኛ ደረጃ ጥቃት ሊደርስበት ይችላል። ሆኖም የተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ለሁለተኛ ደረጃ ጥቃት ከፍ ያለ ተጋላጭነት ያላቸው ሲሆን በተለይም ሴቶች እና ሕፃናት በዚህ ውስጥ ይካተታሉ። በወንጀል ዐይነት ተለይቶ ሲታይም የአካላዊ ጥቃት፣ የወሲባዊ እና ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ እንደዚሁም በቤት ውስጥ የሚፈጸም ጥቃት ሰለባዎች ከሌሎች የወንጀል ዐይነቶች ተጎጂዎች በበለጠ ሁኔታ ለሁለተኛ ደረጃ ጥቃት ተጋላጭነት አላቸው።
ዋና ዋና የሚባሉት የሁለተኛ ደረጃ ጥቃት መገለጫዎች የሚከተሉት ናቸው፦
- ተጎጂዎችን መውቀስ፦ ይህ የጥቃት ሰለባዎችን ለጥቃቱ መፈጸም ምክንያት እንደሆኑ ወይም አስተዋፆ እንዳደረጉ በመቁጠር ኃላፊነት እንዳለባቸው ወይም የጥፋተኛነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ ሲሆን፣ በተለይም ከፍተኛ የአደጋ ሥጋት ባለባቸው ሁኔታዎች (high-risk environment) ውስጥ በሚከሰቱ ጥቃቶች ላይ የሚያጋጥም ነው።
- የደረሰውን ጉዳት ማሳነስ፦ በጥቃት ተጎጂዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት እና ያደረሰውን አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳነስ እንዲሁም ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች የተሰማቸው ስሜት ተገቢ እንዳልሆነ አድርጎ ማቅረብን ያመለክታል፡፡
- ተጎጂዎችን በተደጋጋሚ መጠየቅ፣ መጠራጠር ወይም ተገቢውን እምነት አለማሳደር፦ ጥቃት የደረሰባቸው ተጎጂዎች የሕግ፣ የጤና፣ የሥነ-ልቦና፣ የማኅበራዊ እና ሌሎች ተያያዥ መፍትሔዎችን እንዲሁም ድጋፎችን ለማግኘት ሲሉ በሚያልፉባቸው ሂደቶች ውስጥ ለሚያጋጥሟቸው አካላት ስለደረሰባቸው ጥቃትም ሆነ ስላስተናገዱት የጉዳት ሁኔታ ደጋግመው እንዲያስረዱ ይጠየቃሉ ወይም ይገደዳሉ። ስላጋጠማቸው ጥቃት ወይም ጉዳት ሲያስረዱም በመጠራጠር ወይም ተገቢውን እምነት ባለማሳደር የቃላቸው ትክክለኛነትና ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ እንደገባ እንዲሰማቸው ይደረጋሉ።
- ለሕዝብ ማጋለጥ (Public Exposure):- የተጎጂዎች ጉዳትና ሁኔታ ከተጎጂዎች ፍላጎት፣ ስሜት እና የግላዊነት መብት ጥበቃ በተቃራኒ በመገናኛ ብዙኃን ወይም በሌሎች አካላት ለሕዝብ ሲጋለጥ፣ ተጎጂዎችን ለተጨማሪ የስሜት፣ የሥነ-ልቦና ቀውስ እና ጉዳት ይዳርጋል።
- ማግለልና አድልዎ፦ የጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሰዎች በደረሰባቸው ጥቃት ምክንያት ከማኅበረሰቡ ሊገለሉ ወይም ተለይተው እንዲኖሩ ሊገደዱ፣ ተቃውሞ ሊደርስባቸው፣ የጥላቻ ወይም ያለመፈለግ ስሜት እንዲሰማቸው ሊደረጉ ይችላሉ።
- በቂ ድጋፍ ያለመኖር/ቸል መባል፦ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ከሕግ መፍትሔ ባሻገር በቂ የጤና አገልግሎት እንዲሁም ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ወዘተ. ድጋፎች ያስፈልጓቸዋል። ሆኖም ተጎጂዎች እነዚህን ድጋፎች ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ እንዲሁም ከባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ ለማግኘት አለመቻላቸው ያሉበትን የጉዳት ሁኔታ ከማባባሱ ባሻገር ለተጨማሪ ሥቃይና ጭንቀት ይዳርጋቸዋል፡፡
ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችና ሕፃናት ለሁለተኛ ደረጃ ጥቃት እንዳይጋለጡ ምን ዐይነት ጥበቃና ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል?
የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተፈጻሚነት ያላቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች እና ሰነዶች የሴቶችን እና የሕፃናትን ከጥቃት የመጠበቅ መብት ዕውቅና ይሰጣሉ። ለአብነትም በሕገ መንግሥቱ፣ በአፍሪካ የሰዎችና ሕዝቦች መብቶች ቻርተር የሴቶች መብቶች ፕሮቶኮል (ማፑቶ ፕሮቶኮል) እንዲሁም በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አድሎአዊ ልዩነት ለማስወገድ በተደረገው ስምምነት ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች መሠረት ማንኛዋም ሴት ለሕይወቷ እና ለአካል ደኅንነቷ እንደዚሁም ለሌሎች መብቶቿ ክብር እና ጥበቃ የማግኘት መብት አላት። አግባብነት ያላቸው የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፣ የዓለም አቀፍ የሕፃናት መብቶች ስምምነት እና የአፍሪካ የሕፃናት መብቶችና ደኅንነት ቻርተር ድንጋጌዎች እነዚሁ መብቶች ለሕፃናትም የተጠበቁላቸው መሆኑን ያረጋግጣሉ።
ሀገራት በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስወገድ ብሎም ጥበቃ ለማድረግ ማንኛውንም አስፈላጊ የሕግ፣ የአስተዳደር እና ሌሎች እርምጃዎች መውሰድ የሚገባቸው ሲሆን፣ መብቶቻቸው በተጣሱ ጊዜም ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ፈጣን እና የተሟላ ፍትሕ የማግኘት መብታቸው መከበሩን ማረጋገጥ አለባቸው። ሴቶች እና ሕፃናት ለሁለተኛ ደረጃ ጥቃት እንዳይጋለጡ ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ከላይ ከተጠቀሱት የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች እና ሰነዶች በተጨማሪ እ.ኤ.አ. በ1985 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወጣው የወንጀል እና ሥልጣንን አላግባብ የመጠቀም ድርጊት ሰለባዎች ፍትሕ አሰጣጥ መሠረታዊ መርሖች መግለጫ (Declaration of Basic Principles of Justice for Victims of Crime and Abuse of Power)፣ በሴቶች ላይ የሚደረግ አድሎአዊ ልዩነትን ለማስወገድ በተቋቋመው ኮሚቴ የሴቶችን ፍትሕ የማግኘት መብት አስመልክቶ የተሰጠው አጠቃላይ ምክረ ሐሳብ ቁጥር 33፣ የተ.መ.ድ. ሕፃናት የወንጀል ተጎጂዎችን እና ምስክሮችን የሚያሳትፉ ጉዳዮች ፍትሕ አሰጣጥ መመሪያ (UN Guidelines on justice in matters involving child victims and witnesses of crime) ጠቃሚ መርሖችን ይዘው ይገኛሉ።
ከላይ የተጠቀሱትን ሰነዶች መሠረት በማድረግ ቀጥሎ የቀረቡት መርሖዎች የሴቶችን እና ሕፃናትን ፍትሐዊ ዳኝነትና ውጤታማ ምላሽ የማግኘት መብት በማስከበር ሁለተኛ ደረጃ ጥቃትን ለመከላከል የሚረዱ ናቸው።
- ዕውቅና፣ ርህራሄ እና ክብር፦ የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት መፍትሔ ለማግኘት ወደ ፍትሕ እና ጤና ተቋማት ወይም ሌሎች የአገልግሎት ማእከላት ሲያመሩ የሚጠብቃቸው መስተንግዶ ለጉዳታቸው ተገቢውን ዕውቅና፣ ርህራሄ እና ክብር የሚሰጥ መሆን አለበት። ምላሽ ሰጪ ተቋማት እና ባለሙያዎች ከአድልዎ እና አግላይነት የጸዳ፣ ይልቁንም ለየተጎጂው ልዩ ሁኔታ ስሱነት (sensitivity) ያለው ወይም ልዩ ሁኔታውን ከግምት የሚያስገባ የአያያዝ ሥርዓት ሊከተሉ ይገባል። ለዚህም ሲባል ለፖሊሶች፣ ዐቃብያነ ሕግ፣ ዳኞች፣ የሕክምና እና ሥነ ልቦና ባለሙያዎች እንዲሁም ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማሳደጊያ ስልጠናዎችን መስጠት አስፈላጊ ነው።
- ጥበቃ እና የደኅንነት ዋስትና፦ የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት የመጀመሪያ ደረጃ ጥቃቱን ካደረሰባቸው ግለሰብም ሆነ ከሌሎች አካላት ተጨማሪ ጥቃት፣ የበቀል እርምጃ፣ ትንኮሳ ወይም ማስፈራራት እንዳይደርስባቸው ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ጥበቃ ሊደረግላቸውና የደኅንነት ዋስትና ሊሰጣቸው ይገባል።
- አሳታፊ እና የተፋጠነ ፍትሕ፦ ከአቤቱታ አቀራረብ ጀምሮ ባለው የፍትሕ አስተዳደር ሂደት ውስጥ የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት የሚያገኙት አገልግሎት አሳታፊ እና የተፋጠነ ሊሆን ይገባል። አሳታፊነት ሲባል ተጎጂዎች ሊያውቋቸው የሚገቡ አስፈላጊ መረጃዎችን እንዲያውቁ ማድረግን፣ ያጋጠሟቸውን ክስተቶችና የደረሱባቸውን ጉዳቶች ሳይፈሩና ሳይሳቀቁ እንዲናገሩ ዕድል መፍጠርን እንዲሁም አግባብነት ባለው ደረጃ ሐሳብና አስተያየታቸው እንዲደመጥ እና ዋጋ እንዲሰጠው ማድረግን ይጨምራል። በሌላ በኩል የዘገየ ወይም የተራዘመ የፍትሕ አሰጣጥ ሂደት በራሱ የሁለተኛ ደረጃ ጥቃት ምንጭ በመሆኑ፣ የአቤቱታ አቀራረብ፣ የምርመራ፣ የክስ አቀራረብ እና አሰማም፣ የውሳኔ አሰጣጥና አፈጻጸም ሂደቱ ቀልጣፋ እና ተጎጂዎችን ከተራዘመ የስሜት ወይም የሥነ-ልቦና ቀውስ እና ጉዳት የሚታደግ መሆን አለበት።
- ምስጢራዊነት፦ በምላሽ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ የተጎጂ ሴቶችን እና ሕፃናትን የግላዊነት መብት (privacy) ማክበር ይገባል። ይልቁንም ምስጢራዊነቱ የተጠበቀ የአሠራር ዘዴ በመፍጠር እና በምላሽ አሰጣጥ ሂደቱ የሚሳተፉ ተቋማትን፣ ባለሞያዎችን እና መገናኛ ብዙኃንን በሕግ አግባብ በመቆጣጠር የተጎጂዎችን ስሜት፣ መብት ወይም ደኅንነት የሚጎዱ መረጃዎች አላግባብ እንዳይጋለጡ ማድረግ ያስፈልጋል።
- የጤና እና የሥነ ልቦና አገልግሎት፦ የጥቃት ተጎጂ ሴቶች እና ሕፃናት ከደረሰባቸው አካላዊና ስሜታዊ ጉዳት ለማገገም እና ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው ጤናማ ሕይወት እንዲመሩ ለማስቻል በቂ እና ዘላቂ የጤና እንዲሁም የሥነ ልቦና ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል።
- ውጤታማ እና የተቀናጀ ድጋፍ፦ የጥቃት ተጎጂ ሴቶችና ሕፃናት ለጉዳታቸው ምላሽ ለማግኘት ወይም በተጨማሪ ሥጋት ምክንያት ከመኖሪያቸው ርቀው በሚቆዩበት ጊዜ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ምቹ የሆነ መጠለያ ሊመቻችላቸው ይገባል። እንደዚሁም በተቻለ መጠን ለፍላጎታቸው በቂ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ እና ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ሊቀርብላቸው ይገባል። ከዚህ አንጻር፣ የጥቃት ተጎጂ ሴቶች እና ሕፃናት ጥበቃ እና የምላሽ አሰጣጥ ሂደት በርካታ ተዋንያንን ስለሚያሳትፍ በተቀናጀና ግልጽ በሆነ የቅብብሎሽ ሥርዓት መመራት አለበት።
- ተገቢ ካሳ እና መልሶ ማቋቋም፦ የጥቃት ተጎጂ ሴቶች እና ሕፃናት ለደረሰባቸው ጉዳት ተገቢውን ካሳ የማግኘት መብታቸው ሊከበርላቸው እና በዘላቂነት ተቋቁመው ሰላማዊ ሕይወት የሚመሩበት ሁኔታ ሊመቻችላቸው ይገባል። ለዚህም የተጎጂዎችን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ምቹ የካሳ አከፋፈል ሥነ ሥርዓት መተግበር፣ ከመደበኛ የፍትሕ አስተዳደር መንገዶች በተጨማሪ አማራጭ የፍትሕ፣ የካሳ እና የዘላቂ መፍትሔ ዕድሎችን መጠቀም እንዲሁም ለተጎጂዎች የተቀናጀ የዐቅም ግንባታ ድጋፍ ማድረግ እና በተለያዩ የአሠራር ሂደቶች ውስጥ መብቶቻቸውን በአግባቡ መጠቀም ስለሚችሉበት ሁኔታ የግንዛቤ ማሳደጊያ ትምህርቶችን እና ስልጠናዎችን መስጠት ያስፈልጋል።