የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
ግንቦት 28 ቀን 2014 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በግንቦት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ሁሉን-አቀፍ የግምገማ መድረክ (Universal Periodic Review) ምክረ ሃሳቦች አፈጻጸምን ከማስተዋወቅና ከመቆጣጠር አንጻር የሲቪል ማኅበራት ያላቸውን ሚና የተመለከተ ሁለተኛ ዙር ስልጠና አዘጋጅቷል።
ሁሉን-አቀፍ የግምገማ መድረክ (Universal Periodic Review – UPR) በመንግሥታት የሚመራ፣ አሳታፊና በፍላጎት/ትብብር ላይ የሚመሰረት ሂደት ሲሆን፣ ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራት በሀገራቸው ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ለማሻሻል እና የሰብአዊ መብቶች ግዴታቸውን ለመወጣት የወሰዱትን እርምጃዎች በማስመልከት ሪፖርት እንዲያቀርቡ ዕድል የሚሰጥ ነው። የግምገማውን ሂደት ተከትሎ በግምገማው የተለዩ ክፍተቶችንና ጉድለቶችን ለማሻሻል ምክረ ሃሳቦች ይሰጣሉ። ኢትዮጵያ በሦስት የ UPR ዙሮች (2002፣ 2006 እና 2011 ዓ.ም.) ባቀረበችው ሪፖርት ላይ አስተያየት ተቀብላለች። በ2011 ዓ.ም. በተደረገው ግምገማ ላይ ከ132 ሀገራት 327 ምክረ ሃሳቦች ለኢትዮጵያ የቀረቡ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል ኢትዮጵያ 270 ምክረ ሃሳቦችን ተቀብላ 57ቱን ሳትቀበል ቀርታለች።
ከጥቅምት 17 እስከ 18 ቀን 2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (Office of the High Commissioner for Human Rights) የሁሉን-አቀፍ የግምገማ መድረክ (Universal Periodic Review) ምክረ ሃሳቦች፣ እንዲሁም የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ተቋማት የሚሰጡትን ምክረ ሃሳቦች አፈጻጸም ከመቆጣጠር አንጻር የሲቪል ማኅበራት ያላቸውን ሚና የተመለከተ ስልጠና አዘጋጅተው ነበር። የክትትል ስብሰባውም ይህንን ስልጠና ተከትሎ የተካሄደ ሲሆን፣ ዓላማው የሲቪል ማኅበራትን የሁሉን-አቀፍ የግምገማ መድረክ (Universal Periodic Review) ምክረ ሃሳቦች አፈጻጸም የመከታተል አቅምን የበለጠ ማሳደግ እና ለመከታተል የወሰዷቸውን እርምጃዎች ከሲቪል ማኅበራት ለመስማት ነበር።
የኢሰመኮ የሴቶችና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ በመክፈቻ ንግግራቸው “የምክረ ሃሳቦች አፈጻጸምን አስመልክቶ መንግሥት ሪፖርት የማቅረብ ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለው ቢሆንም የሲቪል ማኅበራት የምክረ ሃሳቦቹን አፈጻጸም አስመልክቶ የራሳቸውን ምልከታ ሪፖርት ለማቅረብ ልዩ ዕድል አላቸው” ሲሉ አስረድተዋል። ኮሚሽነሯ አክለውም የሲቪል ማኅበራት እና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት በሀገራቸው ስላለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ተዓማኒነት ያለው መረጃ በመስጠት በመንግሥት እና በአህጉራዊ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት እንደሚያግዙ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት በተባበሩት መንግሥታት ሁሉን-አቀፍ የግምገማ መድረክ (Universal Periodic Review) ላይ ካላቸው ተሳትፎ ጋር በተገናኘ፤ በ2011 ዓ.ም. በተካሄደው የሦስተኛው ዙር የግምገማ ወቅት፣ እነዚሁ ማኅበራት የተቀናጀ ጥረት በማድረግ ወደ 10 የሚሆኑ ሪፖርቶችን አቅርበው እንደነበር ተገልጿል። የሲቪል ማኅበራት ልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ቢኖርባቸውም ተግዳሮቶችን በመቋቋምና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሲቪል ማኅበራት አዋጅ መሻሻልን ተከትሎ ለኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት የተፈጠረውን የበለጠ ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ከሌሎች ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጋር በመተባበር ጭምር አስተዋጾአቸውን ሊያጎለብቱ እንደሚገባም ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት በአሁኑ ወቅት አገልግሎት ላይ ያሉ የሁሉን-አቀፍ የግምገማ መድረክ (Universal Periodic Review) የመረጃ ቋቶችን በመጠቀም እንደ ኢሰመኮ፣ የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት (Office of the High Commissioner for Human Rights) እና የብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች የድርጊት መርኃ ግብር ጽሕፈት ቤትን (National Human Rights Action Plan Office) ከመሰሉ እና ድጋፍ ሊሰጡ ከሚችሉ ተቋማት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ምክረ ሃሳብ ቀርቧል። በስብሰባው የሲቪል ማኅበራት የሁሉን-አቀፍ የግምገማ መድረክ (Universal Periodic Review) ምክረ ሃሳቦች አፈጻጸምን በተመለከተ ሪፖርት እንዲያቀርቡ የሚያስችል እንዲሁም ተጨባጭ ውጤቶች እና የጊዜ ሰሌዳዎችን የሚያካትት ረቂቅ-እቅድ ተነድፏል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አልባብ ተስፋዬ በመዝጊያ ንግግራቸው፣ “ኢሰመኮ የኢትዮጵያን የሲቪል ማኅበራት የተባበሩት መንግሥታት ሁሉን-አቀፍ የግምገማ መድረክን ምክረ ሃሳቦች አፈጻጸም ለመከታተል እንዲሁም ከዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ጋር እንዲሰሩ ለማገዝ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።