(አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5 ቀን 2013 ..) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎች በሴቶችና በሕፃናት የጤና መብት ላይ ጫና ማሳደሩን ከሐምሌ 21 – ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ፣ በሲዳማ፣ በአማራ እና ጋምቤላ ክልሎች ባካሄደው ፈጣን ዳሰሳ ለማረጋገጥ እንደቻለ ገለጸ፡፡ 

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ዋና አማካሪ ዜናዬ ታደሰ እንደገለጹት፤”የሴቶችና ሕፃናት የጤና መብቶች በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሊጣሱ አይገባም፣ ስለዚህም ችግሩ በቶሎ ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል” ብለዋል፡፡ 

ዋና አማካሪዋ አክለውም የጤና መብቶች የስነተዋልዶ ጤናን ጨምሮ አቅም የፈቀደውን እና በማንኛውም ሁኔታ ወደኋላ የማይመለስ ተገቢውን የጤና አገልግሎት የማግኘት ሰብዓዊ መብቶች የሚጨምር ሲሆን፤ ልዩ ልዩ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ቃልኪዳኖችም የሴቶችና ሕፃናት የጤና መብቶች ልዩ ትኩረት የሚሹ መሆኑን እንደሚተነትኑ ገልጸው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 41 መሰረትም፤ መንግስት የጤና መብቶች የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ይደነግጋል ብለዋል፡፡ 

ይህንኑም መሰረት በማድረግ ኮሚሽኑ ባካሄደው ፈጣን ዳሰሳ፡-

● በተወሰኑ የጤና ተቋማት በተለይ በደቡብ ክልል የነፍሰጡር ሴቶች የቅድመ-ወሊድ ክትትል መቀነስ እና በተወሰኑ ከከተማ ራቅ ባሉ ቦታዎች ለወረርሽኙ በተሰጠው ትኩረት ምክንያት ለቅድመ ወሊድ እና ድህረ ወሊድ ሕክምና የሚላክ አምቡላንስ መኪና ባለመኖሩ ከአጎራባች ወረዳዎች ወደ ከተማ ጤና ተቋማት የሚመጡ ወላድ ሴቶች ቁጥር መቀነሱን ፤ 

● ለምሳሌ በጋምቤላ ክልል በገጠር ቀበሌ የጤና ኬላዎች የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት በመቋረጡ የተነሳ ሴቶች በቤት ውስጥ በመውለድ ምክንያት ለብዙ የደም መፍሰስ ችግር እየተጋለጡ መሆኑን፤

● የሕፃናት ጤናን በሚመለከትም በአንዳንድ ቦታዎች በዘመቻ መልክ ይሰጥ የነበረው ክትባት እንዲቋረጥ መደረጉ፣ የክትባት መድሃኒቶች እጥረት ፣ የኩፍኝ በሽታ ምልክቶች መበራከት፣ ብዙ ቤተሰቦች ከ5 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትን ለሕክምና ማምጣት ማቆማቸው የመሰሉ ችግሮች መፈጠራቸውን ለመረዳት ችሏል፡፡ 

በዳሰሳው የተገኙት ውጤቶች በጤና ተቋማት እየተሰጡ ያሉ አገልግሎቶች በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች እና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት የተደነገጉትን መሰረታዊ መብቶች ከማክበር እንዲሁም ሴቶችና ሕፃናትን በተመለከተ ሊሰጡ የሚገባቸውን ትኩረቶች ከመስጠት አንፃር ክፍተት መኖሩን የሚያሳዩ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ 

ስለሆነም ኮሚሽኑ፡- 

● የቅድመ-ወሊድ ክትትልን ጨምሮ የሴቶች የስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት ለወረርሽኙ በሚሰጥ ትኩረት ሊስተጓጎል የማይገባው በመሆኑ ስለአገልግሎቱ አለመቋረጥ ተገቢውን መረጃ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም የሰው ኃይልና አምቡላንስን የመሰሉ አቅርቦቶችን ማሟላት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራ እንደሚገባ፤ 

የሕፃናት የጤና ክትትልና የበሽታ መከላከል ተግባራት ያለመስተጓጎል፣ ያለመቋረጥና ወደኋላ ያለመመለስ መርሆችን ያከበሩ እንዲሆኑ ለማድረግ የቤት ለቤት እና የዘመቻ የክትባት አገልግሎቶች መልሰው እንዲጠናከሩ፣ የኩፍኝ በሽታ ምልክቶች መበራከታቸውን ከግምት ያስገባ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ፣ የክትባት መድኃኒት አቅርቦት እንዳይቋረጥ እና በወረርሽኙ ምክንያት ወላጆች ሕፃናት ልጆቻቸውን ወደሕክምና ተቋሟት ማምጣት እንዳያቋርጡ ለማድረግ በቂ የግንዛቤ መፍጠር ሥራ መሠራት እንዳለበት፤ምክረሀሳቡን ያቀርባል፡፡