የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት የ9 ወር የሥራ ክንውን ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሚያዝያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. አቅርቧል፡፡ ኮሚሽኑ ባቀረበው የሥራ ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባደራጃቸው ዘጠኝ የትኩረት መስኮች የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ የተገኙ ውጤቶች እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች በዝርዝር ተካትተዋል፡፡
በቀረበው ሪፖርት የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራን በተመለከተ ኮሚሽኑ በዋናው መሥሪያ ቤቱና በከተማ ጽሕፈት ቤቶቹ በ1491 ሰዎች 1680 ጉዳዮች ላይ አቤቱታ የቀረቡለት ሲሆን ከነዚህም መካከል በኮሚሽኑ ሥልጣን ሥር የሚወድቁ 1084 አቤቱታዎችን ተቀብሎ ማስተናገዱ ተገልጿል፡፡ አቤቱታ ከቀረበባቸው ጉዳዮች መካከል አብዛኞቹ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶችን የተቀሩት ደግሞ የኢኮኖሚያዊና የማኅበራዊ መብቶችን የተመለከቱ ናቸው።
ኮሚሽኑ በ48 ማረሚያ ቤቶች እና በ323 ፖሊስ ጣቢያዎች ባካሄደው የክትትል ሥራ ለይቶ ባስቀመጣቸው ግኝቶች እና በሰጣቸው ምክረ ሐሳቦች መሠረት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ እና ያለበቂ ማስረጃ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች መፈታታቸውን፣ የዋስትና መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው መደረጉን፣ ኢ-ሰብአዊ አያያዝ ሲፈጽሙ የነበሩ የተወሰኑ የጸጥታ አባላት ተጠያቂ መደረጋቸውን፣ በመደበኛ ማረሚያ ቤቶች በእስር ላይ ያሉ ሰዎች መብቶች ጥበቃ እና አያያዝ መሻሻል ማሳየታቸው እና ለአብዛኛዎቹ አቤቱታዎች አወንታዊ መፍትሔ እንዲያገኙ መደረጉን ኮሚሽኑ ለምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት ጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል በሪፖርት ዘመኑ ኮሚሽኑ በደረሱት አቤቱታዎችና በራሱ አነሳሽነት በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል፣ በአፋር፣ በሱማሌ፣ በአማራ እና ደቡብ ክልሎች በሚገኙ 59 የተፈናቃይ እና የስደተኞች መጠለያዎች፣ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር የሚኖሩ ተፈናቃዮች እና የተመላሾች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ክትትል አድርጓል፡፡
ከምርመራ ሥራ ጋር በተገናኘ ኮሚሽኑ በጋምቤላ ከተማ በነበረው ውጊያ የተነሳ በደረሱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ ሪፖርት ይፋ ማውጣቱን፤ የሴቶች (ከኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች አንጻር) እና ሕፃናት መብቶች የሚመለከቱ የሕግ ማዕቀፎች እና በአተገባበር ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለመለየት የሚያስችሉ ምርምር/ጥናት መደረጉን፣ በሴቶችና ሕፃናት መብቶች ዙሪያ ፖሊሲ/ሕጎች ላይ የምክር አገልግልት መሰጠቱን እና ያልጸደቁ ስምምነቶች እንዲጸድቁ የውትወታ ሥራ መከናወኑን ለምክር ቤቱ በቀረበው የሪፖርት ማብራሪያ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም በሕገወጥ እና በዘፈቀደ እስር ላይ ትኩረቱን ያደረገ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በሕዝብ ፊት የሚካሄድ ብሔራዊ/ግልጽ የምርመራ መድረክ በሃዋሳ፣ በጂግጅጋ፣ በባሕር ዳር እና በአዳማ ከተማ ተዘጋጅቷል፡፡ በደቡብ ክልል በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቅት እና በድኀረ ምርጫ በወረዳዎች እና ዞኖች የሰብአዊ መብት አያያዝን በተመለከተ ክትትል በማድረግ ሁለት ሪፖርቶች ተዘጋጅተዋል።
በማኅበራዊ እና በኢኖሚያዊ ዘርፍ የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ ሠራተኞች መብቶች አተገባበር ዙሪያ የክትትል ሪፖርት ማውጣቱን እና በሪፖርቱ የተዘረዘሩ ምክረ ሐሳቦች በአዲስ አበባ፣ በባሕር ዳር፣ በሃዋሳ እና በጅማ ከተሞች ተግባራዊ መደረጋቸውን ለመገምገም በተደረገ የምክክር መድረክ ሪፖርቱ ከወጣ በኋላ የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የሠራተኞች መብቶች አጠባበቅ መሻሻላቸውን ለመረዳት መቻሉን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ገልጿል፡፡
ኮሚሽኑ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር የምሥራቅ አፍሪካ ጽ/ቤት (UNOHCHR – EARO) ጋር በመተባበር በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ በሰላም እና ጸጥታ ላይ ከሚሠሩ የሲቪል ማኅበራት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት መሪዎች ጋር የሽግግር ፍትሕን የተመለከተ 15 የመስክ ምክክሮችን አድርጓል። የማኅበረሰብ ምክክሮችን መሠረት በማድረግ፣ የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍን ለማዳበር ይረዳሉ የተባሉት ዋና ዋና ግኝቶች፣ ምክረ ሐሳቦች እና የፖሊሲ ማዕቀፍን በመንደፍም ሆነም በመተግበር ሂደት ውስጥ በአትኩሮት ሊጤኑ የሚገባቸው ዓለም አቀፍ መርሆችን ያካተተ መሪ ሰነድ (Advisory document) ተዘጋጅቶ ይፋ መደረጉ ተነግሯል፡፡
በተጨማሪም በሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የአረጋውያን እና አካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እና ተካታችነት ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ የውትወታ ሥራዎች ተከናውነዋል። ኮሚሽኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ያከናወነውን የአረጋውያን እንክብካቤ ማእከላት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ሪፖርት ይፋ ያደረገውም በዚሁ የሪፖርት ወቅት መሆኑ ተገልጿል።
በተመሳሳይ በሴቶችና ሕፃናት መብቶች ዙርያ የተሠሩ ክትትሎች እና ይፋ ከተደረጉ ሪፖርቶች በተጨማሪ በተለይም በቂ የኑሮ ደረጃ በማግኘት፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን የተመለከቱ ክትትሎች መታቀዳቸውን በሪፖርቱ ተመላክቷል። በሁሉም ክልሎች የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ክትትሎች በሪፖርቱ ወቅት መሠራታቸውን የገለጸው ኢሰመኮ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተለዩ ግኝቶች ላይ ተመሥርቶ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር የውትወታ ሥራ በመሥራት ላይ ማተኮሩ ተገልጿል። በአጋርነት፣ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን እና በተቋም ግንባታ የተሠሩ ሥራዎችም ተጠቅሰዋል። በሰብአዊ መብቶች ትምህርት ዘርፍም በዘጠኝ ወራት በስድስት ክልሎች የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት፣ በሀገር ውስጥ ተፈናቃይ፣ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች እንዲሁም በሴቶች እና ሕፃናት መብቶች ላይ ለሚሠሩ ሲቪል ማኅበራት አባላት በአጠቃላይ 2000 ለሚጠጉ ሰዎች የአሰልጣኞች ስልጠናን ጨምሮ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫና ስልጠናዎች የተከናወኑ ሲሆን፤ በሌላ በኩል በኢንተርኔት አማካኝነት በሚተላለፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርታዊ መልዕክቶች በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ተደራሽ መሆን መቻሉ ተመላክቷል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ባለፉት ዘጠኝ ወራት “በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ግጭት በሰላም ለመቋጨት የተደርገው ስምምነት፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ እና በቤንሻንጉል ክልሎች ያለውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተጀመረው ጥረት፣ የሽግግር ፍትሕን ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችና ምክክሮች፣ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የተወሰዱ የተወሰኑ እርምጃዎች ለምሳሌ በጋምቤላ ክልል፣ እንዲሁም በሃዋሳ፣ በጅግጅጋ፣ በባሕር ዳር እና በአዳማ ከተሞች በመንግሥት ተሳትፎና በሕዝብ ፊት በግልጽ የተካሄዱ ብሔራዊ የምርመራ ሂደቶች፣ የሰብአዊ መብቶች ትምህርትን በመደበኛ ትምህርት ሥርዓት ለማካተት ኮሚሽኑ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር የጀመራቸው ሥራዎች፣ የደቡብ ክልል ምርጫ ከመጠነኛ ሥነ-ሥርዓታዊ ግድፈቶች ውጪ የሰብአዊ መብቶች በተከበሩበት ሁኔታ መካሄዱ ጥሩ ተስፋ ሰጪ እርምጃዎችና ጅማሮዎች መሆናቸውን” ገልጸዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “በአንጻሩ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴና የሰብአዊ መብቶች እንደምታው፣ የዘፈቀደ እስርና በእስር ወቅት የሚደርስ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ፣ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የጸጥታ ኃይሎች የሚወስዱት ተመጣጣኝ ያልሆነ የኃይል እርምጃ፣ በጋዜጠኞች፣ በሚዲያ፣ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ተቃዋሚ ድምጾች ላይ ያነጣጠረ ጥቃትና የቅድመ ክስ እስር፣ ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ላይ የተጣሉ የዘፈቀደ ገደቦች፣ በድርቅ፣ ሕጋዊ ሂደትን ያልተከተለ የቤቶች ፈረሳ እና በግዳጅ ማስነሳት አሳሳቢ ጉዳዮች ሆነው ቀጥለዋል” ሲሉ አብራርተዋል። በተመሳሳይ “በከፍተኛ የኑሮ ውድነት የተነሳ በሕዝብ ላይ የደረሰ እንግልትና የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ጥሰቶች፣ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን (በተለይም የትምህርትና የጤና አገልግሎት) መልሶ ለማቋቋም ገና ብዙ ሥራ የሚጠብቅ መሆኑ እና እነዚህ ሁሉ ችግሮች በሴቶች፣ በሕፃናት፣ በአካል ጉዳተኞችና በአረጋውያን ላይ ተደራራቢ ለሆኑ የመብት ጥሰቶች የሚያጋልጥ መሆኑን” ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል። በተጨማሪም “ኮሚሽኑ የፖሊስ ጣቢያዎችንና ሌሎች መደበኛ ያልሆኑ ሰዎች የታሰሩባቸውን ቦታዎች በቀላሉ ለመጎብኝት አለመቻሉና የበጀት አቅም ውስንነት አሳሳቢ ሆነው እንደቀጠሉ” ገልጸዋል።
በመጨረሻም ዶ/ር ዳንኤል ምክር ቤቱ የኮሚሽኑን ምክረ ሐሳቦች በየደረጃው ባሉ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ተፈጻሚነታቸውን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት በመስጠት ሊሠራ ይገባል ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የተከበሩ የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው ኢሰመኮ በማድረግ ላይ ላለው ጥረት ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበው በሪፖርቱ ላይ በርካታ ዝርዝር አስተያየቶችን ሰጥተዋል። በዚህም መሠረት የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከሰጧቸው ምክረ ሐሳቦች መካከል በአንዳንድ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ በምክር ቤቱ ልዩ ሪፖርት እንዲቀርብ እና ኮሚሽኑ የምክረ ሐሳብ አፈጻጸም በሚሠራበት ወቅት የቋሚ ኮሚቴው ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግለት የሚሉት ይገኙበታል፡፡