የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ለሚገኙ የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት፣ የኪነ ጥበብ/ሥነ ጥበብ ባለሞያዎች፣ ሲቪክ ማኀበራት እና የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች እና የሥራ ኅላፊዎች በግንቦት እና በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም. የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ስልጠናዎችን ሰጥቷል። የተሰጡት ስልጠናዎች በአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች፤ በሕፃናት መብቶች፤ በሕግ ታራሚዎች መብቶች ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡
የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶች ስልጠና
ኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞችን ሰብአዊ መብቶች ለማስከበርና ለማስፋፋት የሚረዱ ስልጠናዎችን በሐረር፣ በጅግጂጋ እና በአዲስ አበባ ከተሞች ለሚገኙ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት አመራሮች እና አባላት በድሬዳዋ እና አዳማ ከተሞች ከሚያዚያ 30 እስከ ግንቦት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. እንዲሁም ከግንቦት 7 እስከ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው አካል ጉዳተኞች እና በአካል ጉዳተኝነት ዙሪያ የሚሠሩ የሲቪክ ማኅበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡ ኮሚሽኑ በሰጠው ስልጠና በዓለም አቀፍ እና በብሔራዊ ደረጃ የተደረሱ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነቶች ላይ ዕውቅና የተሰጣቸው የሰብአዊ መብቶች እሴቶች እና መርሖችን በሰፊው መዳሰስ ተችሏል፡፡
የሕፃናት መብቶች ስልጠና
ኮሚሽኑ በሕፃናት ጥበቃ ላይ ለሚሠሩ የመንግሥት ተቋማት ባለሙያዎች እና የሥራ ኅላፊዎች በሕፃናት መብቶች ዙሪያ ከግንቦት 14 እስከ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው ከደቡብ ክልል ወላይታ ሶዶ እና አርባምንጭ ከተሞች እንዲሁም ከሲዳማ ክልል ለኩ፣ አበላ ቱላ፣ ይርጋለም፣ ዳሌ፣ ወንዶገነት እና አለታ ጭኮ ከተሞች ሴቶች እና ማኀበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተውጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ ስልጠናው ስለሕፃናት መብቶች ዕውቀት ማስጨበጥ፣ የሰብአዊ መብቶች እሴቶችን መሠረት ያደረገ አመለካከትን ማጎልበት እንዲሁም ተሳታፊዎች ያገኙትን ዕውቀትና አመለካከት ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ለማስቻል ያለመ ነው፡፡ በስልጠናውም ተሳታፊዎች በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚስተዋሉ የሕፃናት መብቶች ጥሰቶችን መለየት እና መወሰድ ስላለባቸው የእርምት እርምጃዎች በቡድን ውይይት ሐሳብ እና ልምድ እንዲለዋወጡ አጋጣሚን ፈጥሯል፡፡
የኪነ ጥበብ/ሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ስልጠና
የኪነ ጥበብ/ሥነ ጥበብ ባለሙያዎችን የሰብአዊ መብቶች ዕውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት በማዳበር ለሰብአዊ መብቶች መስፋፋት እና መከበር ያላቸውን ጉልህ ሚና እንዲረዱ እና እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና በሁለት ዙር ለኪነ ጥበብ/ሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡ የመጀመሪያው ዙር ስልጠና በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የኪነ ጥበብ/ሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ማኀበራት ለተውጣጡ ባለሙያዎች ለሶስት ተከታታይ ቀናት በአዳማ ከተማ የተሰጠ ሲሆን በስልጠናው 17 ወንድ እና 4 ሴት በአጠቃላይ 21 ሰልጣኞች ተሳትፈውበታል፡፡ በተመሳሳይ ከግንቦት 28 እስከ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በተሰጠው ስልጠና በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የኪነ ጥበብ/ሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ማኀበራት፣ በግል ከሚንቀሳቀሱ የኪነ ጥበብ/ሥነ ጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኀን የጥናት ማእከል የተውጣጡ 21 ወንድ እና 10 ሴት በአጠቃላይ 31 ሰልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡
የሕግ ታራሚዎች መብቶች ስልጠና
ኢሰመኮ የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት እና ሲቪል ሠራተኞች የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶችን ከማክበር፣ ማስከበር እና ማሟላት አኳያ ያለባቸው ኅላፊነት ላይ ትኩረት ያደርግ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና በቢሾፍቱ ከተማ ከሰኔ 5 እስከ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. እና ከሰኔ 26 እስከ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሁለት ዙር ሰጥቷል፡፡
በመጀመሪያው ዙር ስልጠና በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሥር ከሚገኙት የቃሊቲ የወንዶች እና ሴቶች ማረሚያ ቤቶች የተውጣጡ ሰልጣኞች ተሳትፈዋል፡፡ በሁለተኛው ዙር በተመሳሳይ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ከዝዋይ እና ከሸዋሮቢት ማረሚያ ቤቶች ለተውጣጡ ፖሊሰ አባላት ስልጠናው ተሰጥቷል፡፡
በስልጠናው የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት እና ሲቪል ሠራተኞች፣ የሕግ ታራሚዎች ሰብአዊ መብቶችን አስመልክቶ ያላቸውን ግንዛቤ ለማጎልበት፣ ከአፈጻጸም አንጻር ለሚስተዋሉ ችግሮች ሥረ-ምክንያት የሚሆኑ የዕውቀት፣ የክህሎት እና የአመለካከት ክፍተቶችን በመለየት መፍትሔ በሚሆኑ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
በተጨማሪም የታራሚዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዘ ላይ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸው በደቡብ ክልል ክልል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ሥር ከሚገኘው የጨንቻ ማረሚያ ቤት የተወከሉ የሥራ ኅላፊዎች በምስል እና ገለጻ የተደገፈ ልምዳቸውን ለሰልጣኞች አካፍለዋል፡፡ ይህም በጨንቻ ማረሚያ ቤት ያሉትን መልካም ተሞክሮዎች ለማወቅ ዕድል ከመፍጠር በዘለለ የታራሚዎች አያያዝ የሰብአዊ መብቶች መለኪያዎችን በሚያሟላ መልኩ እንዲሆን ለማድረግ መነሳሳት እንዲፈጠረ ተሳታፊዎች በወቅቱ ገልጸዋል፡፡