የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ኃላፊነታቸውን በራሳቸው ፈቃድ ለለቀቁት የቀድሞ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ እና የቀድሞ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ ነሐሴ 22 ቀን 2017 ዓ.ም. የምስጋናና ዕውቅና መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ዋናው መሥሪያ ቤት አካሂዷል። የኢሰመኮ ዋና መሥሪያ ቤት እና የከተማ ጽሕፈት ቤቶች የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በአካል እንዲሁም በበይነ-መረብ በመርኃ ግብሩ ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ከኢሰመኮ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች የተውጣጡ ሠራተኞች ለተሰናባች ኮሚሽነሮች ምስጋና እና መልካም ምኞታቸውን አቅርበዋል። በቀድሞ ኮሚሽነሮች የአገልግሎት ጊዜ ኢሰመኮ በርካታ ስኬቶችን እንዳስመዘገበ፣ በተለይም የቀድሞ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ኢሰመኮ ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ተልዕኮውን ለመወጣት የሚያግዘውን ፋይናንስ በማፈላለግ እና ለሰብአዊ መብቶች ጠበቃ በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማበርከታቸው ተነግሯል። እንዲሁም የቀድሞ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎች መብቶችን ከማስከበር አንጻር ውጤታማ የውትወታ ተግባራትን በማከናወን መንግሥት የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶችን ለማረጋገጥ አስተዋጽዖ ያላቸውን የሕግ እና የፖሊስ እርምጃዎች እንዲወስድ በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና እንደተጫወቱ ተገልጿል።

የቀድሞ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በመድረኩ ባስተላለፉት መልእክት በተገኙ ስኬቶች ላይ እየጨመሩ በመሄድ ኢሰመኮን ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም የሚተርፍ ተቋም ማድረግ እንደሚገባ በማንሳት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል። አክለውም በሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ እና ከውጭ ሆነው የኢሰመኮን ሥራዎች በመደገፍ የተጎጂዎችን መብቶች በማስከበር ረገድ በትብብር እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል። የቀድሞ ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ በበኩላቸው በሥራ ዘመናቸው አብረዋቸው የሠሩ ባልደረቦቻቸው ላሳዩዋቸው ክብር ምስጋና አቅርበው፤ የኢሰመኮ ሠራተኞች በቀጣይ ለተሻለ አፈጻጸም እንዲጥሩና በሂደቱም የበኩላቸውን እያበረከቱ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ብርሃኑ አዴሎ፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ኢሰመኮ ለተሰናባች ኮሚሽነሮች ውጤታማ ሥራዎች ዕውቅና እንደሚሰጥ እና ወደፊትም በኢትጵያ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ በጋራ እንደሚሠሩ እምነት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም የኢሰመኮ ስኬቶች ከሥራ ኃላፊዎች ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ ሠራተኞች ውጤታማ ቅንጅት ውጤቶች መሆናቸውን በማስታወስ ሥራዎች ሳይቋረጡ እንደቀጠሉ ተናግረዋል።