በኢትዮጵያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አደሎ ጋር ዛሬ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ወቅት አምባሳደሩ ኢሰመኮ ለሰላም ግንባታ የሚያደርገውን ጥረት ያደንቁ ሲሆን፣ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ያላቸውን ድጋፍ እና አድናቆት አሳይተዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኘው የዩኤስ ኤምባሲ ባወጣው መግለጫ አምባሳደር ማሲንጋ “በአርሲ በቅርቡ የተፈጸሙትን ግድያዎች በተመለከተ ኢሰመኮ ላቀረበው ዝርዝር እና ግልጽ ሪፖርት እንዲሁም በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የእስረኞችን መፈታት ለማመቻቸት ያደረገውን ጥረት አሜሪካ እንደምትደግፍ” አጽንኦት ሰጥተውበታል።

ኤምባሲው አክሎም ዩናይትድ ስቴትስ “ኢሰመኮ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተለይም በትግራይ በሚገኙ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች የኢኮኖሚ ማገገምን፣ የነጻ ተቋማት ግንባታን፣ የፍትህ ሥርዓቱን መመለስን፣ ዲሞክራሲን እና ማህበራዊ መልሶ ግንባታ እና ለማስፋፋት የሚያደርገውን ዘላቂ ሥራ በጉጉት ትጠብቃለች” ብሏል።