የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሴቶችና ሕፃናት መብቶች የሥራ ክፍል ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ጥረቶች ያሉበትን ሁኔታ ለመገንዘብ እና ችግሩን ለመቀነስና ለመግታት ሊወሰዱ የሚገባቸው እርምጃዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ከፍትሕ ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሰብአዊ መብቶች ማዕከል ጋር በጋራ በመሆን መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. የባለድርሻ አካላት ውይይት አካሂዷል፡፡ ኢትዮጵያ በተለይም ሴቶችን እና ሕፃናትን ከሕገ-ወጥ ዝውውር እና ብዝበዛ የመከላከል ግዴታን የሚጥሉ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ፈራሚ ሀገር ነች። 

ከእነዚህም መካከል ዋነኞቹ ዜጎች በሕገ-ወጥ መንገድ በማዛወርና ድንበር በማሻገር ወንጀል ውስጥ የሚደርስባቸዉን ከፍተኛ የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ጉዳት ለመከላከል የወጣው ዓለም አቀፍ  ስምምነት እና እና ተያያዥ የሆነው Palermo Protocol ናቸው። (Palermo Protocol፡ A United Nations (UN) protocol to prevent, suppress and punish trafficking in human beings, especially women and children, supplementing the UN Convention against Transnational Organized Crime) በተጨማሪም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ የሚመራ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር የማሻገር ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ምክር ቤት በአዋጅ ቁ/1178/2012 ተቋቁሞ በስሩም በ በፍትሕ ሚኒስቴር የሚመራ ጽሕፈት ቤት ተደራጅቶ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ 

መደበኛ ባልሆነ መንገድ ወደ ተለያዩ የውጭ ሀገራት ለሥራ ፍለጋ የሚደረገው ፍልሰት ተባብሶ በመቀጠሉ ሴቶችና ሕፃናት፣ ጉልበት ብዝበዛ፣ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ እገታን ጨምሮ ለከፍተኛ ሰብአዊ መብቶች ጥሰት እየተጋለጡ ይገኛሉ። የኢሰመኮ ሴቶችና ሕፃናት መብቶች የሥራ ክፍል ኃላፊ  ላምሮት ፍቅሬ ዓለም አቀፍ የሴቶችን ቀን በምናከብርበት ወር ውስጥ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ድንበር ማሻገር በሴቶችና ሕፃናት ላይ ሰብአዊ መብቶች ጥሰት እያደረሰ በመሆኑ ምላሽ ለመስጠት የሚደረጉ ጥረቶችን ውጤታማ ለማድረግ በጋራ መስራት አስፈላጊነትን ለማስታወስ የተዘጋጀ አውደ ጥናት መሆኑን በማስገንዘብ ስብሰባውን አስጀምረዋል።

ላምሮት ፍቅሬ፣ የሴትችና ሕፃናት መብቶች ዳይሬክተር፣ ኢሰመኮ

በስብሰባው ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሠላሳ አንድ (31) የፌዴራል መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የፌዴራልና ክልል ፍትሕ አካላት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተሳትፈዋል፡፡ በውይይቱም ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን የመቆጣጠር ሥራውን አዳጋች ያደረጉ የሕግና የፖሊሲ ክፍተቶችና ሊወሰዱ የሚገባቸው የማሻሻያ እርምጃዎች፣ ለመቆጣጠር በሚደረግ ጥረት ያጋጠሙ አፈጻጸም ተግዳሮቶች፣ ለመደበኛ ፍልሰት ገፊ የሆኑ ሁኔታዎች /pushing factors/ እና የሚደርሰውን የከፋ ሴቶችና ሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ጥሰት ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚደረጉ ጥረቶችን ውጤታማ ለማድረግ ባለድርሻ አካላት በጋራና በተናጠል በቀጣይ ሊያከናውኑ የሚገባቸው ሚና ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡  

በአሁኑ ወቅት ሥራ ላይ የዋለው የመረጃ አያያዝ ጥፋተኞችን ማዕከል ያደረገና ተጠቂ የሆኑትን ሴቶችና ሕፃናት በእድሜና ፆታ የማይለይ መሆኑ፣ ተጠቂዎች የሕግ ከለላ ባለማግኘታቸው በተጠርጣሪዎች ለዳግም ሰለባነት የሚጋለጡበትና የሕግ ሂደቱ በድርድር የሚቋረጥበት አግባብ መኖሩ፣ የወንጀል አይነቱ የፌዴራል ስልጣን በመሆኑና ለክልሎች ውክልና የተሰጠበት አግባብ ወጥና ግልጽ ባለመሆኑ ተጠርጣሪዎችን ተጠያቂነት ከማድረግ አኳያ የአፈጻጸም ክፍተት መኖሩ፣ የተለያዩ ጥረቶች ቢኖሩም በቂ የሰለጠኑና ክህሎት ያላቸው የምርመራ ባለሙያዎች አለመኖር፣ በማኅበረብ ውስጥ ያሉ አመለካከት ችግሮችና በቂ ግንዛቤ አለመኖር ለሴቶችና ሕፃናት ፍልሰት መጨመር አስተዋጽዖ ማድረጋቸው ከተነሱት ተግዳሮቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡ 

የውይይቱ ተሳታፊዎች

መፍትሔዎቹን በተመለከተ ረቂቅ ብሔራዊ የፍልሰት ፖሊሲ ፀድቆ ወደ ተግባር እንዲገባ፣ የተቀናጀ የቅብብሎሽ አሰራር መዘርጋት፣ በፍትሕ አካላት ላይ አቅም ግንባታ እንዲሁም ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተጠናክረው ሊሰሩ፣ በፌደራልና ክልል ፍትሕ ቢሮዎች ግልጽና ወጥ የሆነ ቅንጅታዊ አሰራር በመዘርጋት፣ የወንጀሉ ተጠቂ የሆኑ ሕፃናትና ሴቶችን ማዕከል ያደረገ ሁሉን አቀፍ መልሶ የማቋቋም አገልግሎትን ማጠናከር፣ የተጠቂዎችን የተሰባጠረ መረጃ እንዲሰጥ የሚያስችል የመረጃ ሥርዓት መዘርጋት የሚሉት ተነስተዋል።  

ይህንንም እውን ለማድረግ በአዋጅ ቁጥር 1178/2020 በተቋቋመው የፌደራል ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ስር በመመሪያ ቁጥር 563/2013 የተደራጁትን ስድስት የሥራ ቡድኖች በበላይነት እንዲመሩ ስልጣን የተሰጣቸው ተቋማት በቁርጠኝነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ 

የኢሰመኮ የሕፃናት መብቶች አስተባባሪ ሰላማዊት ግርማይ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሚታዩ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሕፃናት መደበኛ ያልሆነ ዝውውር የሚያስከትለውን የመብቶች ጥሰት ምላሽ ለመስጠት የሚደረጉ ጥረቶችን ሊያዘገዩ ስለሚችሉ ሕፃናት ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ ጥበቃ እንዲደረግላቸው የተቀመጠውን የሕግ ከለላ ለመተግበር መንግሥት ጥብቅ የሕግ አፈጻጸምና ቅንጅታዊ አሰራር ሊከተል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ 

የኢሰመኮ የሕፃናት መብቶች አስተባባሪ ሰላማዊት ግርማይ

በመጨረሻም የኢሰመኮ ሴቶችና ሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ በማጠቃለያ ንግግራቸው “ሀገራችን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተቀብላ ሪፖርት የምታደርግ እንደመሆኑ መጠን መደበኛ ያልሆነ የሰዎች ዝውውር የሚያስከትለው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚብስ በመሆኑ ችግሩን በመቅረፍ ረገድ የምንሰራቸው የመከላከልና ምላሽ የመስጠት ስራዎች ከሰብአዊ መብት ማዕቀፍ አንፃር ማየት እንዲሁም የጉዳዩ ባለቤት የሆኑትን ሴቶችና ሕፃናት በማሳተፍ ሊሰራ ይገባል”  በማለት አሳስበዋል።