በስደተኞች እና ፍልሰተኞች ሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ዙሪያ ያካሄደውን የክትትል ግኝቶች መነሻ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከደቡብ ኦሞ ዞን የሕግና ፍትሕ አካላት ጋር ጥቅምት 27 ቀን 2019 ዓ.ም. በዞኑ ሀመር ቱርሚ ከተማ የምክክር መድረክ አካሄዷል።
በዚህ የምክክር መድረክ ላይ የኢሰመኮ ኮሚሽነሮችና ባለሞያዎች፣ የደቡብ ኦሞ ዞን እና ወረዳ ፍርድቤቶች ፕሬዝደንቶች ፣ የፍትሕ አካላት፣ የፖሊስና ሕግ ማስከበር ተቋማት ኃላፊዎችና ተወካዮች፣ የስደተኞችና ከስደት ተመላሽ አገልግሎት ተቋም ኃላፊዎች እንዲሁም የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ለዚህ የምክክር መድረክ መነሻ የሆነው ሰነድ ኢሰመኮ ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በአርባ ምንጭ፣ ዲመካ፣ ቱርሚ፣ ዳሰነች፣ ያንጋቶም፣ ሃመር፣ ወላይታ ሶዶ እና ሐዋሳ ያካሄደው የክትትል ሥራ ነው።


የኢሰመኮ የሴቶችና ሕፃናት መብት ኮሚሽነር ወ/ሮ አሸነፈች አበበ በመድረኩ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር÷ ኮሚሽኑ ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ስደተኞች እና ፍልሰተኞች ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ልዩ የሥራ ክፍል በማደራጀት የስደተኞችንና የጥገኝነት ጠያቂዎችን ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር ሲሠራ መቆየቱን ገልጸዋል።
የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ የስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች መብቶችን በተመለከተ የሕግ ማስከበርና የፍትሕ አካላት ያላቸውን ግንዛቤ ማሳደግ ነው ያሉት ኮሚሽነሯ፣ በስደተኞች ጥበቃ ዙሪያ ያለውን ዘርፈ-ብዙ ትብብርና ቅንጅት ማሻሻልም ሌላኛው ወሣኝ ግብ መሆኑን አስረድተዋል።


ኢትዮጵያ በብሔራዊ፣ ክልላዊና ዓለም አቀፋዊ የሕግ ማዕቀፎች የገባቸው ግዴታዎች የስደተኞችን ሰብዓዊ ክብርና ደህንነት ማስጠበቅን የሚጠይቁ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት ኮሚሽነሯ፤ ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በግጭት፣ በስደትና በስጋት ምክንያት ከመኖሪያቸው የሚፈናቀሉ በመሆናቸው ለዘረፋ፣ ለብዝበዛ፣ ለእስር፣ ለሕገ-ወጥ ዝውውርና ለተለያዩ የመብት ጥሰቶች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
በተለይም ሴቶችና ሕፃናት ለፆታዊ ጥቃት ጨምሮ ለከፋ አደጋ ተጋላጭ በመሆናቸው፣ የሕግ ማስከበርና የፍትሕ ተቋማት በእስር፣ በማቆያ፣ በምርመራ፣ በፍርድ ሂደትና በማስተላለፍ ወቅት ሕጋዊ ሥነ-ሥርዓቶችንና የሰብዓዊ መብት ጥበቃዎችን የማስከበር ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በክትትሉ ወቅት ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ ከፖሊስ፣ ከፍትሕ ቢሮዎች፣ ከማረሚያ ቤቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ የክትትሉ ዋና ዓላማ መደበኛ ያልሆነ የስደተኞች ቀጣይ እንቅስቃሴ በሚደረግበት ወቅት የሚከሰቱ የጥበቃ ስጋቶችንና የተቋማቱን ምላሽ በመለየት አዎንታዊ መፍትሔ ማስቀመጥ እንደሆነ ተጠቅሷል።


በኮሚሽኑ ባለሙያዎች የቀረቡትን የክትትል ግኝቶች መነሻ በማድረግ በተደረገው ሰፊ ውይይት ግንዛቤን የሚያሳድጉ፣ ኋላፊነት ያለባቸው ተቋማት በአግባቡ እንዲወጡ የሚያበቁ ሃሳቦች ተነስተዋል።
በመድረኩ ማጠቃለያ መልእክት ያስተላለፉት የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞችና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር መሐመድ አህመድ በሂደቱ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ይበልጥ ተጋላጭ በመሆናቸው አስፈላጊው ትኩረት እንዲሰጥ በማንሳት ሁሉም ባለድርሻዎች የየበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አድርገዋል።