የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሲዳማ ክልል ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ከስድስት የወጣት ማህበራት ለተወጣጡ 35 ወጣቶች ከጥቅምት 15-19 ዓ.ም. በሻሸመኔ ከተማ ለአምስት ቀናት የቆየ በሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው ከተሳተፉ ወጣቶች ውስጥ ስምንት የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡

የስልጠናው ዋና አላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ከወጣቶች ጀምሮ ቀስ በቀስ ሰላማዊ ለሆነ ወቅታዊና መፃኢ ትውልድ ምስረታ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ብቃት ለመፍጠር ሲሆን በተለይም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የወጣት ማህበራት አመራሮችን እውቀት፤ ክህሎት እና አመለካከት በመገንባት ሰብአዊ መብቶችን ተግባራዊ ለማድረግ፤ ለመጠበቅ እና ለማስፋፋት የሚያስችል ብቃት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም ስልጠናው ወጣቶች በሰላም በጋራ መኖርን እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ካሉ ልዩነቶችን መሰረት አድርገው የሚከሰቱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን  በመከላከል ሥራ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የማስቻል አላማ ያለው ነው፡፡  

የስልጠናው ይዘት በሶስት ዋና ዋና ክፍሎች  የተከፈለ ሲሆን ሃያ አምስት ክንውኖች አሉት፡፡ የመጀመሪያው ክፍል በመሰረታዊ ሰብአዊ መብቶችና እሴቶች ዙሪያ ላይ ያተኮረ ሲሆን የሰብአዊ መብት ትርጉምን፤ እሴቶችን፤ መርሆዎችን፤  በአገር አቀፍ ፤ አህጉር አቀፍ እና አለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የህግ ማእቀፎችን፤ ግዴታዎችንና ገደቦችን እንዲሁም መብቶችን በማስከበር ረገድ ሃላፊነት ያለባቸውን አካላት የትኞቹ እንደሆኑ ግንዛቤ ያስጨበጠ ነው፡፡  ሁለተኛው ክፍል  ሰብአዊ መብቶችን በኢትዮጵያ ካሉ ነባራዊ ሁኔታዎች አንፃር  የተመለከተ  ሲሆን ሶስተኛው ክፍል ደግሞ ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበርና ለማስፋፋት የሚረዱ ከህሎቶችን ለተሳታፊዎች ያስተዋወቀ ነው፡፡ በተጨማሪም ስልጠናው የተሳታፊዎችን የእርስ በእርስ መማማርን፤ ጥልቅ እሳቤን  እና የእውቀት ፈጠራን የሚያበረታታ አሳታፊና መስተጋብራዊ የስልጠና ዘዴዎችን ተግባራዊ ያደረገ  ነው፡፡

በአጠቃላይ የስልጠናው ውጤት ተሳታፊዎች  በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዙሪያ ሰፊ ግንዛቤ እንዲኖራቸው  እና የእለት ተእለት ሁኔታዎችን ከሰብኣዊ መብት አንፃር እንዲተነትኑ ከማስቻል ባለፈ  ወደመጡበት አካባቢ ሲመለሱ በተቋምም ሆነ በግለሰብ ደረጃ በተግባር ሊወስዱ የሚችሏቸውን እርምጃዎችንና ተግባራትን እንዲለዩ ያስቻለ ነው፡፡ 

ኢሰመኮ ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ተመሳሳይ ስልጠናዎችን በሌሎች ከተሞችም ቀጣይነት ባለው ሁኔታ  ለመስጠት እቅድ አለው፡፡