የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሴቶችና ሕፃናት በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ የሰብአዊ መብቶች አያያዝን ማእከል ያደረገ የውይይት መድረክ ከሚያዝያ 16 እስከ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ አካሄደ። ውይይቱ የጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሴቶችና ሕፃናት በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ያላቸውን መብቶች በማክበርና በመጠበቅ ረገድ ነባራዊ ሁኔታውን ለመዳሰስ በማቀድ የተዘጋጀ ነው። በተጨማሪም ኢሰመኮ በጉዳዩ ዙሪያ ለሚያከናውነው የክትትልና የምርመራ ሥራ አግባብነት ያላቸውን የቅድመ ምርመራ መረጃዎች ከባለድርሻ አካላት ለማሰባሰብ ያለመ ነው።
ለሁለት ቀናት በዘለቀው ዝግጅት ከፌዴራል፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከ10 ክልሎች የተውጣጡ ዳኞች፣ ዐቃብያነ ሕግ፣ ፖሊሶች፣ የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ባለሙያዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች፣ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተወካዮች እና የሴቶች መብቶች ተሟጋቾች ተሳትፈዋል።
በውይይት መድረኩ በኮሚሽኑ ባለሙያዎች የተዘጋጀ የሕግና ፖሊሲ ዳሰሳ ጽሑፍ ቀርቧል። ጽሑፉ የጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሴቶች እና ሕፃናት በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውስጥ ከአቤቱታ አቀራረብ ሥርዓት ጀምሮ፣ በምርመራ ሂደት፣ በክስ አቀራረብና በክስ መሰማት እንዲሁም በድኅረ ፍርድ ሂደት በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ማዕቀፎች የተጠበቁላቸው መብቶችን ከኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ጋር በማነጻጸር የተጠናቀረ ነው፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች ወደ ፍትሕ አካላት አቤቱታ የሚቀርባበቸው የጥቃት ዐይነቶች አነስተኛነት፣ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ከቦታ፣ ከጊዜ፣ ከገንዘብ ዐቅም፣ ከተቋማዊ መዋቅር አንጻር ያለውን ውስን ተደራሽነት፤ የጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሴቶችና ሕፃናት ወንጀልን ከማመልከት ጀምሮ እስከ ድኅረ ፍርድ ባለው ሂደት ስለሚያጋጥሟቸው የመብት ጥሰቶች እና መንስኤዎቻቸው ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም በተቀናጀ የአንድ ማዕከል እና የመጠለያ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ውስጥ ያሉትን ተጨባጭ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎችና አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች፣ አገልግሎቱ ለአካል ጉዳተኞች እና ለአረጋውያን የጥቃት ተጎጂዎች ያለውን ውስን ተደራሽነት፤ ከአዲስ አበባ እና ከሁሉም ክልሎች የመጡ ባለሙያዎች አጋርተዋል። በሌላ በኩል ሴቶችና ሕፃናት በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱን ለመገልገል በሚሞክሩበት ጊዜ የሚገጥሟቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ በሚሠሩ ባለሙያዎች የሚፈጽሙትን ዳግም ጥቃቶች የሚያሳዩ የተበዳይ ታሪኮች ለተሳታፊዎች ቀርበዋል። የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልእክት፣ “ሴቶችና ሕፃናት ጥቃት ተፈጽሞባቸው በወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ በሚገለገሉበት ጊዜ የሚያጋጥማቸው የፍትሕ ተደራሽነት ችግር እና የሥርዓቱ የአሠራር ክፍተቶች ለዳግም ጥቃት እና ለተደራራቢ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋላጭነታቸውን ይጨምረዋል” ብለዋል። አክለውም ይህን ለመከላከል የፍትሕ አካላት አሠራሮቻቸውን እንዲፈትሹ እና የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ጥሪ አድርገዋል፡፡