የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ሠራተኞች ላይ የተሠሩ ጥናቶችን እና የቀረቡለትን በርካታ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግ ያከናወነውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ባለ 58 ገጽ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል። በክትትል ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚሠሩ በተለይም በሃዋሳ፣ ባሕር ዳር፣ አዲስ አበባ እና ጅማ ከተሞች፤ በአጠቃላይ 122 ሠራተኞች (83 ወንድ እና 39 ሴት)፣ 18 የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች፣ 25 ተጠቃሚ ድርጅቶች፣ 19 አግባብነት ያላቸው የመንግሥት ኃላፊዎች፣ 10 ሌሎች ባለድርሻ አካላት እና 6 የሠራተኞች ማኅበራት አመራሮችን በማሳተፍ መረጃዎች ተሰብስበዋል ።
ክትትሉ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መግለጫ፣ በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች ስምምነት፣ በዓለም አቀፉ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት እና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች፣ በዓለም አቀፍ የሥራ ድርጅት ስምምነቶች እና የውሳኔ ሃሳቦች እና ሌሎች ተዛማጅ የሕግ ሰነዶችን ጨምሮ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ-መንግሥት እና በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ላይ እውቅና የተሰጣቸው የሠራተኞች መብቶች ላይ መሰረት በማድረግ መከናወኑ በሪፖርቱ ተብራርቷል፡፡
ሪፖርቱ በግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች መብቶች አተገባበር ላይ ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን ያመላክታል። በተለይም በእነዚህ ኤጀንሲዎች ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች ለሚሠሩት ሥራ በቂ ክፍያ የማያገኙ በመሆናቸው፤ በተለያዩ ሕጎች እውቅና ያገኘው በቂ ክፍያ የማግኘት መብታቸው እየተከበረላቸው እንዳልሆነ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ በአንዳንድ ተጠቃሚ ድርጅቶች በቀጥታ ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች እና በተመሳሳይ መደብና ቦታ በኤጀንሲዎች አማካኝነት ተቀጥረው በሚሠሩ ሠራተኞች መካከል ከፍተኛ የሆነ የክፍያ እና የጥቅማ ጥቅሞች ልዩነት መኖራቸውን ይህም አሠራር ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ የማግኘት መርሕን እንደሚጻረር በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ሠራተኞች በተገደበ የሥራ ሰዓት የመሥራት መብት ያላቸው ቢሆንም የኤጀንሲ ሠራተኞች በተለይም ሴቶችን ጨምሮ የጥበቃ አገልግሎት በመስጠት ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጁ ከተደነገገው በቀን 8 ሰዓት እና በሳምንት 48 ሰዓት ያልበለጠ የመሥራት ግዴታ በላይ ያለትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዲሠሩ እንደሚገደዱ ሪፖርቱ አመላክቷል።
ሠራተኞችን ከጉልበት ብዝበዛ ለመጠበቅ የሚያስችሉ ዕረፍት እና ፈቃድ የማግኘት መብት በሕግ የተረጋገጡ ቢሆንም በጥበቃ ሥራ የተሰማሩት ሠራተኞች የሳምንት የዕረፍት ቀን እንደሌላቸው እና ዕረፍቱን ሊተካ የሚችል የማካካሻ ክፍያ እንደማይከፈላቸው፣ ያለ በቂ ክፍያ በሕዝብ በዓላት እንዲሠሩ እንደሚደረጉ፣ በአንዳንድ ኤጀንሲዎች ሠራተኞቹ የዓመት እረፍት ፈቃዳቸውን ለመውሰድ በቅድሚያ ተተኪ ሠራተኛ እንዲያመጡ እንደሚደርጉ፣ የሕመም ፈቃድ እና የልዩ ፈቃድ እንደማይሰጥ እና የሚወስዱት ፈቃድ ከዓመት ፈቃዳቸው ላይ ተቀናሽ የሚደረግባቸው መሆኑ በሪፖርቱ ከተለዩ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ናቸው። እንዲሁም በሃዋሳ ከተማ በተደረገው ክትትል ሠራተኞች የወሊድ ፈቃድን ከሙሉ ክፍያ ጋር እንደማያገኙ እና ከወሊድ ሲመለሱም በፊት ይዘውት የነበረውን የሥራ መደብ እና ጥቅማ ጥቅም መልሰው ማግኘት እንደማይችሉ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
ምንም እንኳን የኤጀንሲ ሠራተኞች እየተሰማሩባቸው ያሉ የሥራ ዓይነቶች በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 አንቀጽ 10(1) መሰረት እንደተወሰነ ጊዜ ወይም እንደተወሰነ ሥራ የማይቆጠሩ ቢሆንም፤ ሠራተኞቹ የሚፈርሙት የሥራ ውል ግን የተወሰነ ጊዜ የሥራ ውል (የአንድ ወይም የሁለት ዓመት) በመሆኑ ሠራተኞቹን የሥራ ዋስትና እንዳይኖራቸው አድርጓል ።
የመደራጀት መብት ሠራተኞች መብቶቻቸውን በኅብረት ለማስጠበቅ እና የተሻለ የሥራ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያስችል መብት ቢሆንም የኤጀንሲ ሠራተኞች ማኅበራት በተሟላ ሁኔታ አለመቋቋሙ እና ሠራተኞቹ ትርጉም ያለው ቅሬታ የማሰሚያ እና ውጤታማ ፍትሕ የማግኛ ሥርዓት ተጠቃሚ አለመሆናቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡
ከላይ ለተመለከቱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች የሠራተኞች ስለመብቶቻቸው እና መብቶቻቸውን ስለሚያስከብሩባቸው መንገዶች በቂ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑ፣ አብዛኞቹ የኤጀንሲ ሠራተኞች የሠራተኛ ማኅበር የሌላቸው መሆኑ፣ በማኅበር የተጠቃለሉ የኤጀንሲ ሠራተኞች ከግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ጋር የኅብረት ስምምነት ያልተፈራረሙ መሆኑ፣ የአሠሪ እና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የሚመለከታቸው ጉዳዮች የወል የሥራ ክርክሮች ላይ ብቻ የተገደበ መሆኑ፣ አንዳንድ ኤጀንሲዎች የሠራተኞች ማኅበራት አመራሮች ላይ የሚያደርሱት ጫና መኖሩ፣ ለአሠሪና ሠራተኛ ወሳኝ ቦርድ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ፣ ደካማ የቁጥጥር እና ክትትል ሥርዓት መኖር፣ የተለያዩ እና ያልተናበቡ ሕጎች መኖር፣ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር እና ሕጋዊ ያልሆኑ ኤጀንሲዎች መስፋፋት፣ ተጠቃሚ ድርጅቶች ዋና ትኩረታቸው ዝቅተኛ ዋጋ የሚያቀርብ ኤጀንሲ ማግኘት ላይ መሆኑ እንዲሁም ኤጀንሲዎችም ዝቅተኛ ዋጋ የሚያቀርቡ መሆኑ እንደ አብይ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል፡፡
ኢሰመኮ በግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞችን መብቶች በተሻለ ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማስቻል በመብቶች አተገባባር ላይ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን ለማስወግድ ያስችላሉ ያላቸውን ምክረ-ሃሳቦችን በሪፖርቱ አቅርቧል። በተለይም የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጁ የሁለትዮሽ ግንኙነቶችን የሚሸፍን እንጂ የሦስትዮሽ ግንኙነቶችን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን ባለመሆኑ እና ይህም ለሠራተኞች ሰብአዊ መብቶች መጣስ አስተዋጽዖ እያበረከተ በመሆኑ በዚህ ዓይነት የሥራ ግንኙነት ውስጥ የሚሳተፉትን እያንዳንዱን አካላት ግዴታ እና የመንግሥትን ኃላፊነት በግልጽ የሚያስቀምጥ የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲን የሚመለከት ራሱን የቻለ ሕግ እንዲወጣ ወይም የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ይህንን ባካተተ መልኩ እንዲሻሻል አሳስቧል።
የኢሰመኮ ማኅበራዊና ኢኮኖሚ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል፣ በግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች መብቶችን አፈጻጸም በበላይነት የማረጋገጥ ኃላፊነት የመንግሥት ቢሆንም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በተለይም የግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች፣ ከግል ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ሠራተኞችን የሚያገኙ ተጠቃሚ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን እና ሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኢሰመኮ ያቀረባቸውን ምክረ-ሃሳቦችን በመተግበር ለሠራተኞቹ መብቶች መከበር የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።