ውድድሮቹ በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሀዋሳ፣ ሆሳዕና፣ ሚዛን፣ ጋምቤላ፣ አሶሳ፣ ሰመራ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋ እና ጎንደር ከተሞች የተካሄዱ ሲሆን በ10 ክልሎች እና 2 ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ 63 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና 130 ተወዳዳሪ ተማሪዎች ተሳትፈውበታል፡፡

በውድድሮቹ ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው መምህራን፣ ወላጆች እና የትምህርት ቢሮ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው ተወዳዳሪዎቹን አበረታተዋል፡፡

የምስለ ፍርድ ቤት ውድድር ተማሪዎች ተገቢው ስልጠና ከተሰጣቸው በኋላ ምናባዊ በሆኑ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ ተመስርተው አመልካች እና ተጠሪ በመሆን የቃል እና የጽሑፍ ክርክር የሚያደርጉበትና፣ በሕግና የሰብአዊ መብት ባለሞያዎች የሚዳኙበት ከሞላ ጎደል የመደበኛ ፍርድ ቤት ክርክር ሥርዓትን የሚከተል አስተማሪ የውድድር አይነት ነው፡፡

የመጀመሪያው የምስለ ፍርድ ቤት ውድድር ከስምንት ክልሎች እና ከሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች የተውጣጡ 35 ትምህርት ቤቶችንና 80 ተማሪዎችን ያሳተፈ ሲሆን፣ ሁለተኛው በክልል ደረጃ በአስር ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መካከልና በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ እነዚህን ክልሎች በሚወክሉ አሸናፊ ተማሪዎች መካከል የሚካሄድ ይሆናል፡፡

የምስለ ፍርድ ቤት ውድድሩ ስለ ሰብአዊ መብቶች፣ ስለ ፍትሕ አስተዳደር እና ዳኝነት ግንዛቤን በመፍጠር የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን ለመከላከል እና ጥሰቶቹ በሚከሰቱበት ወቅት ማረሚያ የሚሆኑ የሕግ ሥርዓቶችን ለማስተማር እና ለማስተዋወቅ የሚዘጋጅ ነው። የተማሪዎች የምስለ ፍርድ ቤቶች ውድድር እና መሰል ዝግጅቶች ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርትን ለማዳበር ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ ሲሆን፣ ታዳጊ ተማሪዎች በሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ለመሳተፍ ያላቸውን ፍላጎት ለማሳደግ አስተዋጽዖ ያደርጋል።

በተደረጉት ውድድሮች 1ኛ እና 2ኛ የወጡ 24 ተወዳዳሪ ቡድኖች ከግንቦት 15 እስከ ግንቦት20 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የቃል ክርክር ውድድር ለማለፍ የጽሑፍ ክርክራቸውን ለኢሰመኮ በመላክ የሚወዳደሩ ይሆናል፡፡