የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ለሦስተኛ ጊዜ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምስለ ችሎት (Moot Court) ውድድር የመጀመሪያ ምዕራፍ  ማጣሪያ ከመጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በአስር ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ሲካሄድ ቆይቶ ለሀገር አቀፍ ውድድሩ ተሳታፊዎችን በመለየት ተጠናቋል፡፡

በየክልሉ እና ከተማ አስተዳደሮቹ በተካሄዱት የማጣሪያ ውድድሮች ከ72 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 144 ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በማጣሪያ ውድድሩ የቃል ክርክር በሁሉም ተሳታፊ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ሚያዝያ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. የተካሄደ ሲሆን የየክልላቸውን ውድድር ያሸነፉ 12 ተወዳዳሪ ትምህርት ቤቶች በሀገር አቀፉ ውድድር ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የጽሑፍ መከራከሪያ ለኢሰመኮ እንዲያስገቡ ተደርጓል። በዚሁ መሠረት ለኮሚሽኑ የደረሱት የጽሑፍ መከራከሪያዎች በከፍተኛ ባለሙያዎች ተመዝነዋል። በምዘናው ከደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ ከሐረሪ፣ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ከሲዳማ ክልሎች እንዲሁም ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የተሳተፉና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ስምንት ትምህርት ቤቶች ለሀገር አቀፍ የምስለ ችሎት ውድድር ማለፋቸው ተረጋግጧል። ስምንቱ ቡድኖች የሚሳትፉበት የሩብ፣ የግማሽ እና የፍጻሜ ዙር ውድድሮች ከግንቦት 12 እስከ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳሉ።

የምስለ ችሎት ውድድሩ ምናባዊ በሆነ የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ (Hypothetical Case) ላይ በመነሳት ተማሪዎች የአመልካች እና የተጠሪ ወገንን በመወከል የጽሑፍ እና የቃል ክርክር የሚያደርጉበት ከሞላ ጐደል የመደበኛ ፍርድ ቤት ክርክር ሥርዓትን የሚከተል አስተማሪ የውድድር ዓይነት ነው፡፡ የምስለ ችሎት ውድድሩ ሕግን በመተላለፍ የተጠረጠሩ ወጣት ልጆች እና ከዚህ ጋር ተያይዘው በሚነሱ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥን ይሆናል።

በየክልሎቹ እና ከተማ አስተዳደሮቹ በተካሄዱ የማጣሪያ ውድድሮች ተወዳዳሪ ተማሪዎችም ሆኑ ውድድሮቹን የተከታተሉ ሌሎች ተማሪዎች እና የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ አካላት ስለ ሰብአዊ መብቶች ይበልጥ እንዲያውቁ እና ለሌሎች ሰዎች መብቶች እንዲቆረቆሩ መነሳሳትን የፈጠሩ ነበሩ፡፡