የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሱማሌ ክልል ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አገልግሎት ከሚሰጡ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ለተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ከታኅሣሥ 17 እስከ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ ስልጠና ሰጠ፡፡
ኢሰመኮ ከሰኔ 2013 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም. ድረስ ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ ባደረገበት ወቅት የሶማሌ ክልል እ.ኤ.አ. ከ2022 – 2025 በሥራ ላይ የሚውል የዘላቂ መፍትሔ ስትራቴጂ ሰነድ መቅረጹ በክልል ደረጃ ለተፈናቃዮች የዘላቂ መፍትሔ ለማመቻቸት ምቹ አጋጣሚ የሚፈጥር በመሆኑ የተፈናቃዮችን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከማሻሻል አንጻር እንደመልካም ተሞክሮ እንደሚመለከተው መጥቀሱ የሚታወስ ነው። የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ሰብአዊ መብቶች መጠበቅና ሁኔታቸውን ማሻሻል ብሔራዊ ቁርጠኝነት የሚሻ እና የሁሉንም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ተሳትፎ እና ርብርብ የሚጠይቅ ነው።
ስልጠናውም በዋናነት መንግሥታዊ በሆኑና መንግሥታዊ ባልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማቶች ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች እና የሥራ ኃላፊዎች በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ያላቸውን ዕውቀት ለማጎልበት ያለመ ነበር፡፡ እንዲሁም ተሳታፊዎች መሠረታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች እሴቶች በተለይም ሰብአዊ ክብር፣ እኩልነት፣ አድሎ አለመፈጸም እና ፍትሐዊነት ከአገልግሎት ሰጪዎች ተግባር ጋር ያላቸውን ትስስር በተመለከተ የተሳታፊዎችን ዕውቀት እና አመለካከት ለማዳበር የሚያስችሉ ክንውኖችን ያካተተ ነበር፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎች የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በቅድመ መፈናቀል፣ መፈናቀል እና ድኅረ መፈናቀል ወቅት በዓለም-አቀፍ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፎች ስለተሰጧቸው መብቶች፣ ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ጋር በተያያዘ የመንግሥት ግዴታዎች እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ኃላፊነትን በተመለከተ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ስልጠናው ምቹ አጋጣሚን ፈጥሯል።
በተለይም ከምዝገባ እና ሰነድ ማግኘት፣ የሰብአዊ ድጋፍ በቂነት፣ የተፈናቃዮች ደኅንነት፣ ተጋላጭ ለሆኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ልዩ ጥበቃ እና ድጋፍ ማድረግ፣ ውጤታማ የሆነ ዘላቂ መፍትሔ ከማፈላለግ እንዲሁም ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ አገልግሎት አሰጣጥን ተግባራዊ ከማድረግ ጋር በተገናኘ የሚታዩ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን ለመለየት እና ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላቸውን ስልት የመንደፍ ክህሎት በስልጠናው በተግባር እንዲለማመዱ ለማድረግ ተችሏል፡፡
በስልጠናው ወቅት ተሳታፊዎች ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ለአደጋ የተጋለጡ እና ብዙውን ጊዜ ለመብቶቻቸው መከበር የተለየ ድጋፍ እና ጥበቃ ካልተደረገ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጅ እንደሚሆኑ መገንዘባቸውን እና በዕለት ተዕለት አገልግሎት አሰጣጣቸው በስልጠናው ያገኙትን የሰብአዊ መብቶች ዕውቀት፣ አመለካከት እና ክህሎት በመጠቀም ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ ያላቸውን ተነሳሽነት ገልጸዋል፡፡