አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአዲስ አበባ ፖሊስ ስር በወንጀል መከላከልና ምርመራ ዘርፍ ለተሰማሩ 28 የፖሊስ አባላት የ5 ቀናት ስልጠና ሰጠ፡፡ ስልጠናው ከሰኔ 20 -24 2014 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ የተሰጠ ሲሆን የስልጠናው ተሳታፊዎች ከሁሉም የአዲስ አበባ ከተማ ክፍለ-ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች የተውጣጡ ነበሩ፡፡

ስልጠናው በዋናነት የፖሊስ አባላትን ሰብአዊ መብቶችን የማክበርና የማስከበር አቅም ለመገንባት ያለመ ሲሆን ተሳታፊዎች መሰረታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች እሴቶችን በተለይም ሰብአዊ ክብር፣ እኩልነት፣ ነፃነት፣ አድሎ አለመፈጸም እና ኃላፊነት የመሳሰሉት የሰብአዊ መብቶች እሴቶች ከፖሊስ ሥራ ጋር ያላቸውን ትስስር አስመልክቶ ያላቸውን እውቀትና አመለካከት ለማዳበር የሚያስችሉ ክንውኖችን ያካተተ ነበር፡፡ በተጨማሪም ስልጠናው ተሳታፊዎች  ከዋና ዋና የፖሊስ ኃላፊነትና ተግባራት (ማስቆምና መፈተሽ፣ እስር፣ ምርመራ፣ ብርበራ) ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩና የተያዙ ሰዎች በዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች መሰረት ስላሏቸው መብቶች እንዲሁም ስለኃይል አጠቃቀም መርሆዎቹ ያላቸውን እውቀትና አመለካከት ለማሳደግ ያለመ ነበር፡፡ ከዚህም ባለፈ ተሳታፊዎች ከፖሊስ ሥራና ኃላፊነት በተለይም ከተጠርጣሪዎችና የተያዙ ሰዎች መብቶች ጋር በተያያዘ የሚታዩ አሳሳቢ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን ለመለየትና ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላቸውን ስትራቴጂ የመንደፍ ክህሎት በስልጠናው በተግባር እንዲለማመዱ ለማድረግ ተችሏል፡፡

በባሕር ዳር፣ ጅማና ሃዋሳ ከተሞች

ኢሰመኮ ቀደም ሲል፤ ከሰላም አብሮነት እና መቻቻል አንጻር በባሕር ዳር፣ ጅማና ሃዋሳ ከተሞች ለሚገኙ የወጣቶች ማኅበራት በሰጠው የሰብአዊ መብቶች የአሰልጣኞች ስልጠና መሰረት ስልጠናውን የወሰዱ የወጣት ማኅበራቱ አባላት በየከተሞቻቸው ለሚገኙ ሌሎች ወጣቶች ስልጠናዎችን ሰጡ፡፡ በዚህም በሦስቱም ከተሞች ሁለት ሁለት ስልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን በአጠቃላይ 69 ሴቶች እና 123 ወንዶች በድምሩ 192 ወጣቶች በስልጠናዎቹ ላይ ተሳትፈዋል።

ስልጠናው በኢትዮጵያ ውስጥ ከወጣቶች ጀምሮ በሂደት ሰላማዊ ለሆነ ማኅበረሰብ ምስረታ አስተዋጽዖ የሚያደርግ ብቃት የመፍጠር አላማን ያነገበ ሲሆን ወጣቶች ሰብአዊ መብቶችን ተግባራዊ ለማድረግ፤ ለመጠበቅ እና ለማስፋፋት የሚያስችል ብቃት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ በተጨማሪም ስልጠናው ወጣቶች በሰላምና በጋራ መኖርን እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ካሉ ልዩነቶች በመነሳት የሚከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በመከላከል ሥራ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የማስቻል አላማ ያለው ነው፡፡  

ስልጠናው በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች፤ ሰብአዊ መብቶችን በመረዳት፣ ሰብአዊ መብቶችን ከግጭት ጋር በማዛመድ በመተንተን እና መሰረታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች ክህሎቶችን በተለይም የራስን መብት ለመጠየቅና ለሌሎች መብቶች ለመቆም የሚያስችሉ ክህሎቶችን በመለማመድ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

አዲስ አበባ

ኢሰመኮ ሰብአዊ መብቶችን መሰረት ያደረገ አሰራርን (Human Rights Based Approach) አስመልክቶ ከተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከኮሚሽኑ ለተውጣጡ 22 ባለሙያዎች የአራት ቀን ስልጠና ሰጠ፡፡ ስልጠናው ከሰኔ 20  እስከ ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደ ሲሆን በልማት እና ሰብአዊ መብቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በመዳሰስ ሰልጣኞች ሰብአዊ መብቶችን መሰረት ያደረገ አሰራርን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አቅምን እንዲያጎለብቱ ለማስቻል የታለመ ነበር፡፡

በዚህም ስልጠናው ሰልጣኞች ስለድህነት፣ ልማት እና ሰብአዊ መብቶች ያላቸውን ግንዛቤ በማስፋት ሰው ተኮር ለሆነ ልማት አሰተዋጽዖ የሚያደረጉበትን ብቃት ለመፍጠር የሚያስችሉ ርዕሰ ጉዳዮችና ክንውኖች የተካተቱበት ነበር፡፡ በተጨማሪም ስልጠናው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አገልግሎት አሰጣጥ በሰብአዊነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆንና ተቋማዊ አሰራራቸው በመከባበር እና ፍትሐዊነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በማድረግ ለሰብአዊ መብቶች እውን መሆን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲወጡ አቅማቸውን ማጎልበትን ዓላማ ያደረገ ነበር፡፡

ባሕር ዳር 

ኢሰመኮ ከሰኔ 27 እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በባህር ዳር ከተማ ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ደቡብ ጎንደር ዞን፣ አዊ ዞን፣ ምዕራብ ጎጃም ዞን እና ጎንደር ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ 32 ተሳታፊዎች በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በሚሰሩበት ተቋም አማካይነት ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚደረግ የሰብአዊ ድጋፍ እና ጥበቃ አገልግሎት ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸው ናቸው፡፡ ተሳታፊዎቹ ከትምህርት መምሪያ፣ ጤና መምሪያ፣ ፖሊስ መምሪያ እንዲሁም ከአደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የተውጣጡ ነበሩ፡፡

የስልጠናው ዓላማ መንግሥታዊ በሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ያላቸውን እውቀት፣ አመለካከት እና ክህሎት በማዳበር፣ ለሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሚሰጡት አገልግሎት ሰብአዊ መብቶችን መሰረት ያደረገ እንዲሆን ማስቻል ነበር፡፡