የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከኢንተርናሽናል ሚዲያ ሰፖርት (International Media Support) ጋር በመተባበር ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እና የጥላቻ ንግግር መቆጣጠርን አስመልክቶ ለፌዴራልና ለክልል ፍርድ ቤቶች ዳኞች፣ ዐቃቢያነ ሕግ እና የፖሊስ አባላትን ጨምሮ ከተለያዩ የሚዲያ ባለድርሻ አካላት ለተውጣጡ ባለሙያዎች በሁለት ዙር ያዘጋጀውን ስልጠና ኀዳር 27 እና ታኀሣሥ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሰጥቷል።

ስልጠናው የፍትሕ እና የሚዲያ ተቆጣጣሪ አካላት ሐሳብን በነጻነት በመግለጽ መብት እና የጥላቻ ንግግርን በመቆጣጠር ረገድ ተገቢውን ሚዛን እንዲጠብቁ የሚያስችላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ነው።

የስልጠናው ተሳታፊዎች

በስልጠናው ሐሳብን በነጻነት ለመግለጽ  ጥበቃ በሚያደርጉ ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፎችና ሌሎች መሠረታዊ ሰነዶች ላይ ማብራሪያ ቀርቧል። በተያያዘም ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ፍልስፍናዊ መሠረቶች፣ የነጻነቱ ይዘቶችና በመብቶቹ ላይ ሊጣሉ የሚችሉ ገደቦችና ገደቦቹ ሊያሟሏቸው ስለሚገቡ የሕጋዊነት፣ የአስፈላጊነት እንዲሁም የተመጣጣኝነት መርሖች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። ሌላኛው የስልጠና ክፍል የጥላቻ ንግግርን አስመልክቶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ዕውቅና በተሰጠው የራባት የድርጊት መርኃ ግብር (The Rabat Plan of Action) ውስጥ አንድን ንግግር የጥላቻ ንግግር ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመለየት እንዲያግዙ የተቀረጹ 6 መሠረታዊ መለኪያዎች ላይ ያተኮረ ነበር። መለኪያዎቹ በዋነኝነት ንግግሩ የተደረገበትን ዐውድ፣ ተናጋሪው በማኀበረሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት፣ ንግግሩ ግጭት የማነሳሳት ዓላማ ያለው ስለመሆኑ፣ የንግግሩ ይዘት፣ የስርጭቱ መጠን እንዲሁም በንግግሩ ምክንያት ጉዳት የመድረስ ዕድሉን የተመለከቱ መሆናቸው ተገልጿል።

ተሳታፊዎች ባካሄዱት ውይይት ብሔራዊ የሕግ ማዕቀፎቹ፤ በቅርብ ጊዜ የጥላቻ ንግግር እና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅን ጨምሮ  የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ  እና  የወንጀል ሕጉን ከዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መለኪያዎች አንጻር ያላቸው የመጣጣም ሁኔታ ተዳሷል።

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል

የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል የፍትሕ አካላት የጥላቻ ንግግርን የተመለከቱ ጉዳዮችን ሲከታተሉ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በማያጣብብ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያላቸውን መርሖችና መለኪያዎችን ያገናዘቡ መሆን እንዳለባቸው አስረድተዋል።  አያይዘውም ኮሚሽኑ ለፍትሕ አካላት የሚሰጣቸውን የግንዛቤ ማስፋፊያ ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።