የአካል ጉዳተኞችን ወይም አረጋውያንን የተመለከቱ ንግግሮች ሲባል ምን ማለት ነው?
ንግግር ማለት በቃል፣ በጽሑፍ፣ በምስልና ሥዕል፣ በቅርጻ ቅርጽ እና በሌሎች ተመሳሳይ መንገዶች መልእክትን የማሰራጨት ተግባር ነው (የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 1185 /2012 አንቀጽ 2 (1))፡፡ ማንኛውም ሰው የአካል ጉዳተኞችን ወይም አረጋውያንን ለመግለጽ ወይም ሁኔታቸውን ለማስረዳት ወይም እንደምሳሌ ለመጠቀም የሚያደርገው ማናቸውም ንግግር የአካል ጉዳተኞችን ወይም አረጋውያንን የሚመለከት ንግግር ነው፡፡ ስለሆነም ማንኛውም ሰው በተለይም በማኅበረሰብ ውስጥ የመሪነት፣ የኃላፊነት እና የአስተማሪነት ሚና ያላቸው ሁሉ የሚያደርጓቸው ንግግሮች እና የቃላት አጠቃቀም አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን የሚያዋርዱ፣ ለሥነ ልቦና ጉዳት የሚዳርጉ ወይም በተለያየ ምክንያት ለመድልዎ እና ለጥቃት የሚዳርጉ ሊሆኑ አይገባም። ይህ የሕግ ጥበቃ በሕገ-መንግሥቱና በዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተረጋገጡ የአካል ጉዳተኞችንና የአረጋውያንን ሰብአዊ መብቶች መሰረት ያደረገ ነው።
ተገቢ ያልሆኑ የቃላት አጠቃቀሞች ሲባል ምን ማለት ነው?
አዋራጅ ወይም ክብረ-ነክ ቃላት (Derogatory Terms) የአረጋውያንን ወይም የአካል ጉዳተኞችን ሰብአዊ ክብር የሚነኩ፣ የሚያገሉ፣ የሚተናኮሱ በስድብ ወይም በልዩ ልዩ አነጋገር ሊገለጹ የሚችሉ ናቸው፡፡ መንግሥትና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰብአዊ መብቶችን ከማስከበርና ከማሟላት አንጻር እና ሁሉኑም ሰዎች በእኩል ደረጃ ለማገልገል ያላቸው ብቃትና ቁርጠኝነት ከሚለካባቸው መንገዶች አንዱ አካታችና ከሚያንቋሽሹ አዋራጅ ወይም ክብረነክ ቃላት የጸዳ ፤ በሰብአዊ መብቶች መርሆች ላይ የተመሰረተ ንግግር ማድረግ መቻል ነው፡፡
ተገቢ ያልሆኑ ቃላት ለማስወገድ ምን የሕግ ማዕቀፍ አለ?
ኢትዮጵያ ባጸደቀችው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት ከተደነገጉ ግዴታዎች መካከል፤ ሀገራት ጎጂ፣ ልማዳዊና ከስምምነቱ ጋር የሚቃረኑ ሕጎች፣ አሠራሮችና ልማዳዊ ድርጊቶችን ማስወገድ እንዳለባቸው የሚደነግገው አንዱ ነው (የስምምነቱ አንቀጽ 4 (1) /ለ)፡፡ ኢትዮጵያ የስምምነቱን አፈጻጸም ለሚከታተለው ኮሚቴ እ.ኤ.አ. በ2016 ባስገባችው የመጀመሪያ ሪፖርት ላይ ተመስርቶ ከኮሚቴው ለኢትዮጵያ ከተሰጡ ምክረ ሃሳቦች መካከል በኢትዮጵያ የቤተሰብ እና የፍትሐ ብሔር ሕግ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ ክብረ-ነክ ቃላት እንዲወገዱ ጠይቋል፡፡ (የስምምነቱ ተከታታይ ኮሚቴ ምክረ ሃሳብ 6፣ እ.ኤ.አ. 2016)፡፡ በተመሳሳይ በተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ሦስተኛው ሁሉን አቀፍ ወቅታዊ ግምገማ ላይ ኢትዮጵያ እነዚህን ክብረ ነክ ቃላት ያሉባቸውን ሕጎች እንድታሻሻል የሚጠይቅ ምክረ ሃሳብ ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይ የሚደርሰውን መድልዎና መገለል ለማስወገድ የሚያስችሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ተመላክቷል (ሦስተኛው ሁሉን አቀፍ ወቅታዊ ግምገማ፣ ምክረ ሃሳብ ቁጥር 163.263)፡፡
ተገቢ ያልሆኑ ቃላትን በምን መለየት ይቻላል?
ተገቢ ያልሆኑ ቃላትን መለየት ከምንችልባቸው መንገዶች መካከል አንደኛው የተለያዩ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተግባቦቶችን ከወቅቱ የሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የፖሊሲ፣ የሕግና የሰብአዊ መብቶች አውድ ጋር ማገናዘብ ነው። አወንታዊና አሉታዊ (ተገቢ እና ተገቢ ያልሆኑ) ቃላትን ለመለየት እንደማጣቀሻ ከሚያገለግሉ የሕግና የፖሊሲ ሰነዶች መካከል የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕገ መንግሥት፣ የአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት አዋጅ ቁጥር 568/2000፣ የፌዴራል መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014፣ የተ.መ.ድ. የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት፣ የማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ፣ የአፍሪካ አረጋውያን መብቶች ፕሮቶኮል ይገኙበታል፡፡
ሁለተኛው መንገድ በዘርፉ ላይ የሚሰሩ የመንግሥት አካላትን፣ ማኅበራትንና የጉዳዩ ባለቤት የሆኑትን ግለሰቦች ማማከር ሌላው አማራጭ ነው፡፡
አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን የሚመለከቱ የአማርኛና የእንግሊዝኛ አወንታዊ እና አሉታዊ አባባሎች የተወሰኑት ከዚህ በታች ቀርበዋል፡፡
አረጋውያንን ለመጥራት ልንጠቀምባቸው የሚገባ አወንታዊ አባባሎች / Proper terminologies used when referring to older persons ምንድን ናቸው?
አረጋውያን (አረጋዊት፣ አረጋዊ)፣ ሴት አረጋውያን፣ ወንድ አረጋውያን፣ አዛውንት፣ የዕድሜ ባለፀጋ/ባለፀጎች | Older Persons, Older Women/Men, Senior Citizens, The Elderly |
አካል ጉዳተኞችን ለመጥራት ልንጠቀምባቸው የሚገባ አወንታዊ አባባሎች/Proper terminologies used when referring to persons with disabilities ምንድን ናቸው?
አካል ጉዳተኛ | A Person with Disability |
ጉዳት አልባ | A Person without Disability/Non-Disabled Person |
ዐይነ ሥውር | Blind |
መስማት የተሳናት/የተሳነው | Deaf |
ማየትና መስማት የተሳነው/የተሳናት | Deaf-Blind |
አከላዊ ጉዳት ያለባት/ያለበት | A Person with Physical Disability |
የሥጋ ደዌ ተጠቂ | A Person affected by Leprosy |
የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባት/ያለበት | A Person with Intellectual Disability |
የማኅበረ-ሥነ-ልቦና ጉዳት ያለባት/ያለበት | A Person with Psycho-social Disability |
ልናስወግዳቸው የሚገባ አሉታዊ አባባሎች/Derogatory terms ምንድን ናቸው?
አካለ ጎዶሎ፣ አካለ ስንኩል፣ እውር፣ ደንባራ፣ ደንቆሮ፣ ዲዳ፣ ሽባ፣ አንካሳ ፣ በሽተኛ፣ ቆማጣ፣ ቁምጥና ያለበት/ያለባት፣ ድኩማን፣ ድውይ፣ የአዕምሮ ዘገምተኛ፣ ቀሰስተኛ፣ እብድ፣ ቂል፣ ጅል (የተለያዩ የአካል ጉዳት አይነቶችን ለመግለጽ) ጤነኛ ወይም ሙሉ አካል ያለው (ጉዳት አልባዎችን ለመግለጽ)፣ የጃጀ/ች፣ ሼባ፣ አሮጊት፣ ሽሜ-ጉጉ (አረጋውያንን ለመግለጽ) ወዘተ | Handicapped, Crippled, , Lame, Mentally retarded, feeble-minded, Dull, Dumb, Mad, Insane, Crazy (when referring to different types of disabilities) Normal or Able-bodied (When Referring to Persons without disabilities), Fogey, Senile (when referring to older persons), etc |