የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሽግግር ፍትሕ እና ኪነ-ጥበብ በሚል ርዕስ ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ ኮሚሽኑ ሰብአዊ መብቶችን ያገናዘበ የሽግግር ፍትሕ ለማስፈን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ከሚያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት መካከል አንዱ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የትምህርት ተቋማት፣ የኪነ/ሥነ-ጥበብ ማኅበራት ተወካዮችና የኪነ-ጥበብ/ሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል።

ውይይቱ እውነተኛ፣ አሳታፊ፣ አካታች፣ ሀገራዊ ዐውዱን ከግምት ውስጥ የሚያስገባ እና የሰብአዊ መብቶች መርሖችን እና ድንጋጌዎችን ያከበረ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ፣ ይህም እንዲሳካ ኪነ-ጥበብ/ሥነ-ጥበብ እንደ አንድ ዘርፍ መሥራት የሚችላቸውን ተግባራት ለመለየት እና ለመመካከር ያለመ ነው፡፡

በውይይት መድረኩ አካታችና ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ የሽግግር ፍትሕን ለማስፈን ኮሚሽኑ እያከናወነ ስላለው ሥራ እና ከተመድ የሰብአዊ መብቶች ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከተለያዩ ማኅበረሰቦች ጋር ባደረጓቸው ምክክሮች የለዩዋቸው ዋና ዋና ግኝቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ሁሉንም የማኅበረሰብ አካላት ያካተተ የሽግግር ፍትሕን ለማስፈን ኪነ-ጥበብ/ሥነ-ጥበብ ስላለው ሚና ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢሰመኮ አካታች፣ አሳታፊ እና ተጎጂዎችን ያገናዘበ የሽግግር ፍትሕን ለማስፈን እያካሄደ ያለው የማኅበረሰብ ውይይቶች አበረታች መሆኑን ጠቁመው፣ ኪነ-ጥበብ/ሥነ-ጥበብን በመጠቀም መሠራት የሚችሉ ሥራዎችን በማስተባበርና በመተግበር ረገድ ኀላፊነት ያለባቸው አካላትን በዝርዝር ለይተዋል፡፡ በምክክር መድረኩ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅቱ እና ሂደቱ የሰብአዊ መብቶች መርሖችን ያከበረ እና ተጎጂዎችንና የተለያዪ የማኅበረሰብ አካላትን ማሳተፉን ማረጋገጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ተግባር እንደሆነ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ኢሰመኮ ሰብአዊ መብቶች ባህል የሆነባት ኢትዮጵያን ለመፍጠር በማለም ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እና በአጋርነት እንደሚሠራ ጠቁመው፣ የኪነ-ጥበብ/ሥነ-ጥበብ ዘርፍን እንደአንድ አጋር በመውሰድ አማካሪ ቡድን አቋቁሞ እየሠራ እንደሆነ አስታውሰዋል። እንዲሁም ኢሰመኮ የሽግግር  ፍትሕ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘላቂ ሰላም፣ ማኅበረሰባዊ ዕርቅ እና ፈውስ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ የተለያዩ ሥራዎች እየተገበረ መሆኑን ገልጸው ከኪነ-ጥበብ/ሥነ-ጥበብ ዘርፉ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር አካታች፣ አሳታፊ፣ ተጎጂዎችን ያማከለ፣ ሀገራዊ ዐውዱን ከግምት ውስጥ ያስገባ እና የሰብአዊ መብቶች መርሖችን እና ድንጋጌዎችን ያከበረ የሽግግር ፍትሕ ማስፈን በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ የቡኩላቸውን ጉልህ አስተዋፆ ማበርከት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡