የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለያዩ አካባቢዎች በመንግሥት እና በታጠቁ ኃይሎች በሲቪል ሰዎች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ጥቃቶችን በቅርበት በመከታተል ላይ ይገኛል። 

ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በምዕራብ ወለጋ ዞን ግምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በመንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (በተለምዶ ‘ኦነግ ሸኔ’) ታጣቂዎች መካከል ሲደረግ ከነበረው ውጊያ ጋር በተያያዘ በታጣቂው ቡድን በአካባቢው በሚኖሩ ሲቪል ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት በሰው ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡ አሁንም በአካባቢው ከፍተኛ የፀጥታ ስጋት በመኖሩ ምክንያት ነዋሪዎች በአፋጣኝ ድጋፍ እንዲደርስላቸው በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ 

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ መንግሥት በሲቪል ሰዎች ላይ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይፈጸም አስፈላጊ የሆኑ የመከላከል እርምጃዎችን እንዲወስድ፣ በማንኛውም ሁኔታ ሲቪል ሰዎች የጥቃት ዒላማ እንዳይደረጉ ተገቢ የሆነ ጥንቃቄና ጥበቃ እንዲያደርግ፣ እንዲሁም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያፈላልግ አሳስበዋል።