የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በሶማሌ ክልል የእስረኞችን አያያዝ በተመለከተ የተወሰነ መሻሻል የታየባቸው ቦታዎች ቢኖሩም፤ አሁንም ብዙ ማሻሻያዎች የሚስፈልጋቸው ጉዳዮችና ቦታዎች መኖራቸውን ገለጸ። ኮሚሽኑ መጋቢት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. በጅግጅጋ ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች ያደረገውን ፈጣን ክትትል ጨምሮ በተደጋጋሚ ጊዜያት በክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች የሚገኙ የፖሊስ ጣቢያዎችን እና ማረሚያ ቤቶችን በመጎብኘት፣ የእስረኞችን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ በተመለከተ ክትትል አድርጓል፤ ከእስረኞች እና የፖሊስ መምሪያዎች እና የማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎች፣ እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የክልሉ የሕግ አስከባሪ እና የአስተዳደር አካላት ጋር ተወያይቷል።
በክትትሉ ከተጎበኙት ቦታዎች በተለይም በጅግጅጋ ከተማ ካውንስል ፖሊስ መምሪያ በተለምዶ ሃቫና ተብሎ በሚታወቀው የተጠርጣሪዎች ማቆያ እና በ 04 ቀበሌ አቅራቢያ የሚገኘው የካውንስሉ ማቆያ የተጠርጣሪዎች አያያዝ እጅግ አሳሳቢ ነው።
በእነዚህ እስር ቤቶች ተጠርጣሪዎች ንፅህናቸው ባልተጠበቀ እና በጣም በተጨናነቁ ክፍሎች ለጤና ጎጂ በሆነ መልኩ እንደሚያዙ፣ ከፍተኛ የምግብ እጥረት መኖሩን እና በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሕጻናት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 172 መሰረት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በዋስ እንዲለቀቁ ቢጠበቅም፤ ከዚህ በተቃራኒ ከ 18 አመት በታች ያሉ ሕጻናት እስረኞች አካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች ጋር ተቀላቅለው እንደሚያዙ ኮሚሽኑ ተመልክቷል። እንዲሁም በጅግጅጋ ከተማ 04 ቀበሌ አቅራቢያ በሚገኘው የካውንስሉ ማቆያ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች የቤተሰብ ጉብኝት መከልከል፣ ፍርድ ቤት በጊዜ ያለመቅረብና በተወሰኑ እስረኞች ላይ ድብደባም ጭምር እንደደረሰባቸው ኮሚሽኑ ከታሳሪዎች አሳማኝ ምስክርነት ተቀብሏል።
ኮሚሽኑ ከሚመለከታቸው አካሎች ጋር በግንባር ካደረገው ውይይት በተጨማሪ በታኅሣሥ 8 ቀን እና መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ለሚመለከታቸው የከተማው እና የክልሉ አስተዳደር አካላት በተጻፈ ደብዳቤ ከላይ የተጠቀሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በአስቸኳይ እንዲታረሙ ምክረ ሃሳቦችን አቅርቦ ነበር። በተለይም የሃቫና ፖሊስ ጣቢያ ካለበት አስቸጋሪ ሁኔታ አንጻር በአፋጣኝ እንደሚዘጋ በተደጋጋሚ ለኮሚሽኑ ቃል የተገባ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ተግባራዊ አልሆነም።
ከሀቫና ፖሊስ ጣቢያ እስረኞችን ወደ ጎዴ ማረሚያ ቤት በመላክ የጣቢያውን በእስረኞች መጨናነቅ ለመቀነስ የተሞከረ ቢሆንም፤ ይህ የተደረገው ከእስረኞች እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በቂ ምክክር ሳይካሄድ መሆኑን እና የጎዴ ማረሚያ ቤት በራሱ ከፍተኛ መጨናነቅ ያለበት በመሆኑ ታሳሪዎች ቅሬታቸውን ለኮሚሽኑ ገልፀዋል። በጎዴ ማረሚያ ቤት 14 ክፍሎች ሲኖሩ ጉብኝቱ በሚደረግበት ጊዜ 470 እስረኞች ይገኙ ነበረ።
በወንጀል ውስጥ ገብተው በመገኘታቸው በፍርድ ቤት እስራት የተፈረደባቸውና ብዛታቸው ከ 50 በላይ የሆኑ ሕፃናት በጎዴ ማረሚያ ቤት ለአካለ መጠን ከደረሱ እስረኞች ጋር ተቀላቅለው የሚገኙ በመሆኑና ይህም በኢፌዴሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 36(3) ላይ ወጣት አጥፊዎች (ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት) አካለ መጠን ከደረሱ እስረኞች ተለይተው መያዝ እንዳለባቸው የተደነገገውን የሚጥስ በመሆኑ አፋጣኝ ትኩረትና መፍትሄ የሚሻ ነው፡፡
በሌላ በኩል ኮሚሽኑ በክልሉ ውስጥ ተዘዋውሮ ክትትል ባደረገባቸው የፖሊስ መምሪያዎች የሚገኙ ተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ የተደረጉ መሻሻሎች እንዳሉም ተመልክቷል። በተለይም ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ቢያንስ በአንድ ጣቢያ በተወሰኑ ታሳሪዎች ላይ ድብደባ ስለመፈጸሙ ቢገለጽም፤ ስልታዊና የተስፋፋ አካላዊ ጥቃት ስለመኖሩ አይደመጥም። እንዲሁም አቅም በፈቀደ መጠን ተጨማሪ የማቆያ ቦታዎችን በማዘጋጀትና በእስረኞች ሰብአዊ አያያዝ በተለይ በጅግጅጋ ከተማ በሚገኙት የዞን እና የክልል ፖሊስ ጣቢያዎች አበረታች እርምጃዎች ታይተዋል።
እነዚህ አበረታች እርምጃዎች በሁሉም የእስር ቦታዎች እንዲስፋፉና በተለይም የንጽህና ችግር እና የቦታ ጥበት መጨናነቅ ለመቅረፍ፣ የቤተሰብ ጉብኝት መብት በሁሉም ቦታዎች በተሟላ መንገድ ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ታሳሪዎች ፍርድ ቤት በጊዜው መቅረባቸውንና የጥፋተኛ ፖሊስ አባሎችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ተገቢውን እርምጃዎች ሁሉ መውሰድ ያስፈልጋል።
በተጨማሪም በጅግጅጋ ካውንስል ፖሊስ መምሪያ ስር የሚገኙ በወንጀል ነክ ጉዳዮች ተሳታፊ ናቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሕጻናት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 172 መሰረት በአፋጣኝ በዋስ ሊለቀቁ ይገባል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የሶማሌ ክልላዊ መንግስት ሰብአዊ መብቶችን በማክበር እና በማስከበር ረገድ በወሰዳቸው እርምጃዎች የታዩ መሻሻሎች የሚያበረታታ መሆኑን“ ገልጸው፣ “በተለይ ወንጀል ውስጥ ገብተው የተገኙ ሕፃናት እስር ጉዳይ ልዩ ትኩረት እና ፈጣን እርምጃ ያስፈልገዋል” ብለዋል።