የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሶማሌ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል እና በአማራ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ ለስደተኞች አገልግሎት ከሚሰጡ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ለተውጣጡ ከ50 በላይ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ከጥር 15 እስከ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በድሬዳዋ እና ቢሾፍቱ ከተሞች በስደተኞች ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ስልጠና ሰጥቷል።  

በኢትዮጵያ ከሚኖሩት ስደተኞች መካከል ከ50% በላይ የሚሆኑት ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አካል ጉዳተኞች እና አረጋዊያን ናቸው፡፡ ምንም እንኳን በ2011 ዓ.ም. በወጣው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1110/2011 አንቀጽ 38 ለእነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች መንግሥት ልዩ ፍላጎታቸውን መሠረት ያደረገ እገዛ እንደሚያደርግ የተገለጸ ቢሆንም፣ አተገባበሩ ውስንነቶች ይስተዋላሉ።

ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው የዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች እውቅና የተሰጣቸውን ‘የእኩልነት/equality’ እና የ‘ምክንያታዊ ማመቻቸት/reasonable accommodation’ መርሆችን ባገናዘበ መልኩ፣ በመንግሥት እና በተራድኦ ተቋማት ለስደተኞች የሚቀርቡ የሰብአዊ ድጋፎችም ሆኑ ሌሎች አገልግሎቶች አካታች፣ ተደራሽ እና ሰብአዊ ክብራቸውን እና ደኅንነታቸውን በጠበቀ መልኩ መሆናቸውን ሊያረጋግጥ ይገባል። 

ስልጠናው በዋናነት መንግሥታዊ በሆኑና መንግሥታዊ ባልሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማቶች ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያዎች እና የሥራ ኃላፊዎች በስደተኞች ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ያላቸውን እውቀት ለማጎልበት ያለመ ነው። በተጨማሪም ተሳታፊዎች ከስልጠናው መሠረታዊ የሆኑ የሰብአዊ መብቶች እሴቶች በተለይም ሰብአዊ ክብር፣ እኩልነት፣ አድሎ አለመፈጸም፣ ኃላፊነት እና ፍትሐዊነት ከአገልግሎት ሰጪዎች ተግባር ጋር ያላቸው ትስስር ላይ እውቀት እና አመለካከታቸውን ለማዳበር እንዲችሉ አድርጓል፡፡

በተያያዘም ከምዝገባ እና ሰነድ ማግኘት፣ የሰብአዊ ድጋፍ በቂነት፣ የስደተኞች ደኅንነት፣ ተጋላጭ ለሆኑ ስደተኞች ልዩ ጥበቃ እና ድጋፍ ማድረግ፣ ውጤታማ የሆነ ዘላቂ መፍትሔ ከማፈላለግ ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመለየት እና ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላቸውን ስልት የመንደፍ ክህሎት በተግባር እንዲለማመዱ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ተሳታፊዎች በስልጠናው ያገኙትን የሰብአዊ መብቶች እውቀት፣ አመለካከት እና ክህሎት በመጠቀም ተግባራዊ እርምጃ ለመውሰድ ተነሳሽነት እንዳደረባቸው ገልጸዋል፡፡