የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከጥቅምት – ታኅሣሥ ወር 2016 ዓ.ም. ባሉት ሦስት ወራት የሰብአዊ መብቶች ዕውቀትን፣ አመለካከትን እና ክህሎትን የሚያዳብሩ አስራ ስድስት ስልጠናዎችን ለወጣቶች፣ ለሃይማኖት አባቶችና ለሀገር ሽማግሌዎች፣ ለአካል ጉዳተኞች ማኅበር አባላት፣ ለማረሚያ ቤት ፖሊሶች፣ ለፖሊስ አባላት እና አመራሮች፣ ለሲቪል ማኅበራት እና ለመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች እንዲሁም ለግብረ-ገብ ትምህርት መምህራን ሰጥቷል፡፡ የተሰጡት ስልጠናዎች በአካል ጉዳተኞች፣ በሴቶች፣ በተጠርጣሪዎች፣ በሕግ ታራሚዎች መብቶች እንዲሁም በሰብአዊ መብቶችና የሽግግር ፍትሕ እንዲሁም በሰብአዊ መብቶች ትምህርት ሥነ-ዘዴ ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡

ለወጣቶች የሰብአዊ መብቶች ስልጠና ከሰላም፣ አብሮነት እና መቻቻል አንጻር

ለወጣቶች የሰብአዊ መብቶች ስልጠና ከሰላም፣ አብሮነት እና መቻቻል አንጻር

ኢሰመኮ ከሰላም፣ አብሮነት እና መቻቻል አንጻር የወጣቶች ሚናን ለማሳደግ ያለመ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና በመቀሌ ከተማ ከሚገኙ የተለያዩ የወጣት ማኅበራት ለተውጣጡ 34 ወጣቶች በመቀሌ ከተማ ከታኅሣሥ 8 – 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ሰጥቷል፡፡ ስልጠናው ወጣቶች ስለመሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች፣ እንዲሁም እንደግለሰብ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ ለሰላም፣ ለመቻቻል እና ለአብሮነት ሊኖራቸው ስለሚገባ ሚና እና ኃላፊነቶች የነበራቸው ዕውቀት እና አመለካከት እንዲዳብሩ ዕድል ፈጥሯል፡፡ 

ሰብአዊ መብቶችን እና የሽግግር ፍትሕን የተመለከተ የወጣቶች ስልጠና

ኢሰመኮ ዮዝ አዌርነስ ኤንድ ማይንድሴት ግሮውዝ (Youth Awareness and Mindset Growth -YAMG) ከተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ፅንሰ ሐሳብ፣ ሂደቶችና አላባዎችን በተመለከተ ወጣቶች በቂ ዕውቀት እንዲያገኙ እና በሂደቱ ለመሳተፍ ተነሳሽነት እንዲያዳብሩ፤ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ከአምቦ፣ ከሃዋሳ፣ ከመቱ፣ ከኒው ጀነሬሽንና ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲዎች ለተውጣጡ 32 የዩኒቨርሲቲ ሰላም ፎረምና የተማሪዎች መማክርት አመራሮችና አባላት የአሰልጣኞች ስልጠና በአዳማ ከተማ ከታኅሣሥ 8 እስከ 12 ቀን 2016 ዓ.ም. ሰጥቷል። ስልጠናው የሌሎች ሀገራት የሽግግር ፍትሕ ተሞክሮዎች የቀረቡበት ሲሆን የወጣቶችን ጉልህ ሚና ለማሳደግ ተግባራዊ ልምምዶችን እንዲያደርጉ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ሰልጣኞችም በስልጠና ያገኙትን ዕውቀት እና ተሞክሮ ለየዩኒቨርሲቲያቸው ተማሪዎች ለማካፈል ቃል ገብተዋል፡፡

ሰብአዊ መብቶችን እና የሽግግር ፍትሕን የተመለከተ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ስልጠና

በአዲስ አበባ ከተማ በተሰጠው ስልጠና በከተማዋ ከሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት የተወጣጡ 21 የሃይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል

ኢሰመኮ በሽግግር ፍትሕ ፅንሰ ሐሳብ እና ሂደቶች እንዲሁም ከሰብአዊ መብቶች ጋር ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በቂ ዕውቀት እንዲያገኙ እና በሂደቱ የሚጠበቅባቸውን ጉልህ ሚና ለመወጣት ይችሉ ዘንድ ደረጃውን የጠበቀ የስልጠና መምሪያ በማዘጋጀት በድሬዳዋ ከተማ ከታኅሣሥ 3 – 5 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በአዲስ አበባ ከታኅሣሥ 9 – 11 ቀን 2016 ዓ.ም. እንዲሁም በአሶሳና ቦንጋ ከተሞች ከታኅሣሥ 16 – 18 ቀን 2016 ዓ.ም. የአሰልጣኞች ስልጠናዎችን ሰጥቷል፡፡ በድሬዳዋ ከተማ በተሰጠው ስልጠና በሐረሪና በድሬደዋ ከተሞች ከሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት የተወጣጡ 32 የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል። በአዲስ አበባ ከተማ በተሰጠው ስልጠና በከተማዋ ከሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት የተወጣጡ 21 የሃይማኖት አባቶች የተሳተፉ ሲሆን በአሶሳ ከተማ በተሰጠው ስልጠና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት የተወጣጡ 36 የሃይማኖት አባቶች ተሳትፈዋል። በተመሳሳይ በቦንጋ ከተማ በተሰጠው ስልጠና ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ከከፋ ዞን ባህል ምክር ቤት (የሀገር ሽማግሌዎች) እና ከቤንች ሸኮ ዞን ባህል ምክር ቤት የተወጣጡ 32 የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል፡፡

በሐረሪና በድሬደዋ ከተሞች ከሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት የተወጣጡ 32 የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች

ስልጠናዎቹ በኢትዮጵያ ወቅታዊ በሆነው እና ሊተገበር በታሰበው የሽግግር ፍትሕ ሂደት ትኩረት በመስጠት በፅንሰ ሐሳቡ፣ ዐውዶቹ እና ጠቀሜታው ላይ ዕውቀት ለማስጨበጥ እና ግንዛቤ ለማስፋት ያለሙ ሲሆን፤ የሃይማኖት አባቶችንና የሀገር ሽማግሌዎችን ጉልህ ሚና ለማሳደግ ተግባራዊ ልምምዶችን አድርገዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በተሰጠው ስልጠና ላይ የተገኙት የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ፣ የሽግግር ፍትሕ ሐሳብና አተገባበር ከሰብአዊ መብቶች ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ገልጸው፤  የሽግግር ፍትሕን በኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ እንደማኅበረሰብ በሀገራችን ያሳለፍናቸውን ግጭቶችና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን እውነታን በማፈላለግ፣ በይቅርታ፣ በካሳና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ዳግም ለሌሎች ግጭቶችና የመብቶች ጥሰት ምክንያት በማይሆኑበት ሁኔታ ለመቋጨት ዕድል የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ለሽግግር ፍትሕ ሂደቱ መሳካት ሃይማኖታዊና ማኅበረሰባዊ ተቋማት የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የአካል ጉዳተኞች መብቶች ስልጠና

ኮሚሽኑ የአካል ጉዳተኞች ሰብአዊ መብቶችን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የአካል ጉዳተኞች ማኅበራት እና ከሰሜን ሸዋ ዞን የአካል ጉዳተኞች ፌዴሬሽን ለተውጣጡ 40 የማኅበራት አመራሮችና አባላት ከጥቅምት 5 – 9 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው የሰብአዊ መብቶች ዕሴቶች እና መርሖች እንዲሁም ዓለም አቀፍ እና ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች መብቶችን የተመለከቱ ሰነዶች በሰፊው ተዳስሰዋል፡፡ በተጨማሪም በስልጠናው ተሳታፊዎች ለማኅበራቸው አባላት እና ተጠቃሚዎች የሚሰጡት አገልግሎት ሰብአዊ መብቶችን መሠረት ያደረገ እንዲሆን የሚያግዝ ዕውቀት እና አመለካከትን የሚገነቡ ይዘቶችና ተግባራዊ መልመጃዎች ተካተዋል፡፡

የሴቶች መብቶች ስልጠና

ኢሰመኮ የሴቶችን መብቶች በተመለከተ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለግዴታ ተቋማት ያለባቸውን ግዴታ እንዲወጡ የሚያግዝ ስልጠና ከኅዳር 3 – 7 ቀን 2016 ዓ.ም.  ለአምስት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ ሰጥቷል፡፡ ተሳታፊዎቹ ከአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ፍርድ ቤቶች የተውጣጡ 34 ሠራተኞች ናቸው፡፡ ስልጠናው ስለሴቶች መብቶች ዕውቀት ማስጨበጥ፣ አመለካከትን ማጎልበት እንዲሁም ተሳታፊዎች ያገኙትን ዕውቀትና አመለካከት ወደ ተግባር እንዲቀይሩ ለማስቻል ያለመ ነበር፡፡ በስልጠናው በኢሰመኮ ክትትል የተገኙ የሴቶች መብቶች ጉዳዮች እና ከሥርዓተ-ጾታ እኩልነት ጋር በተገናኘ በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ሁሉ-አቀፍ የግምገማ መድረክ ለኢትዮጵያ መንግሥት የተሰጡ ምክረ ሐሳቦችን በተመለከተ ጠለቅ ያለ ገለጻ እና ውይይት ተደርጓል፡፡ በስልጠናውም ተሳታፊዎች የሴቶች መብቶች ጥሰቶችን የመለየት ክህሎት ያዳበሩ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች በቡድን ውይይት ሐሳብ እንዲለዋወጡ እና ስልት እንዲነድፉ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል፡፡

የሕግ ታራሚዎች መብቶችና አያያዝ በተመለከተ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና

በሻሸመኔ ከተማ በተሰጠው ስልጠና ከዶዶላ፣ ከምሥራቅ ባሌ፣ ከምሥራቅ አርሲ፣ ከደሎመና እና ከባሌ ማረሚያ ቤቶች የተውጣጡ 36 የማረሚያ ቤት ፖሊሶች እና አመራሮች ተሳትፈዋል
በሻሸመኔ ከተማ በተሰጠው ስልጠና ከዶዶላ፣ ከምሥራቅ ባሌ፣ ከምሥራቅ አርሲ፣ ከደሎመና እና ከባሌ ማረሚያ ቤቶች የተውጣጡ 36 የማረሚያ ቤት ፖሊሶች እና አመራሮች ተሳትፈዋል

ኮሚሽኑ የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት የታራሚዎችን ሰብአዊ መብቶችን ከማክበር፣ ማስከበር እና ማሟላት አኳያ ያለባቸውን ኃላፊነት በተመለከተ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና በጋምቤላ እና በሻሸመኔ ከተሞች ከኅዳር 10 – 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ሰጥቷል፡፡ በጋምቤላ ከተማ የተሰጠው ስልጠና ተሳታፊዎች ከጋምቤላ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን እና ከጋምቤላ ከተማ፣ ከአኝዋክ፣ ከኑዌር እና ከማጃንግ ብሔረሰብ ዞን ማረሚያ ቤቶች የተውጣጡ 35 የማረምያ ቤት ፖሊሶች እና አመራሮች ናቸው። በሻሸመኔ ከተማ በተሰጠው ስልጠና ከዶዶላ፣ ከምሥራቅ ባሌ፣ ከምሥራቅ አርሲ፣ ከደሎመና እና ከባሌ ማረሚያ ቤቶች የተውጣጡ 36 የማረሚያ ቤት ፖሊሶች እና አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡ በስልጠናዎቹ ላይ በታራሚዎች አያያዝ የመልካም አፈጻጸም፣ ልምድ እና አሠራር ልምዶችን በማጋራት የስልጠናው ተሳታፊዎች ባለው ነባራዊ ሁኔታም ቢሆን ለታራሚዎች የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በተሻለ መልኩ መሥራት እንደሚቻል የተረዱ ሲሆን ለሰብአዊ መብቶች መከበር እንዲሠሩ ተነሳሽነት አሳድረዋል፡፡

የተጠርጣሪዎች መብቶችና አያያዝ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና

ኢሰመኮ ፖሊሶች ከሥራቸው ጋር ተዛማጅ ስለሆኑ የሰብአዊ መብቶች ዕሴቶች ምንነት እና ተግባራዊነት፤ የተጠርጣሪዎች መብቶች እና አያያዝን የተመለከቱ የሰብአዊ መብቶች ደረጃዎች እንዲሁም የፖሊስ ተጠያቂነትን በተመለከተ ዕውቀታቸውን፣ አመለካከታቸውን እና ክህሎታቸውን ለመገንባት ያለሙ ስልጠናዎችን በሰመራ እና በመቀሌ ከተሞች ሰጥቷል፡፡ ከኅዳር 10 – 14 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰመራ ከተማ በተሰጠው ስልጠና ከአፋር ክልል የተወጣጡ 35 የፖሊስ አባላትና አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን፤ ከታኅሣሥ 17 – 19 ቀን በመቀሌ ከተማ በተሰጡ ሁለት ስልጠናዎች ደግሞ ከትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ 70 የፖሊስ አባላትና አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ ፖሊስ የሰዎችን መብቶች እና ነጻነት በመጠበቅ፣ የሕዝብን ሰላምና ጸጥታ በማስከበር እንዲሁም የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ የሰው ልጆች ያለሥጋት በሰላም እንዲኖሩ ከፍተኛ እና የማይተካ ሚና እንዳላቸው በመረዳት ተጠርጣሪዎችን በሚይዙበትና በቁጥጥር ሥር በሚያውሉበት፣ የወንጀል ምርመራ በሚያደርጉበት እንዲሁም የኃይልና የጦር መሣሪያ በሚጠቀሙባቸው በእያንዳንዱ ጊዜያት ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚገቡ መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች ላይ ጥልቅ ግንዛቤ አዳብረዋል፡፡ በተጨማሪም ስልጠናዎቹ ተሳታፊዎች መልካም ተሞክሮዎቻቸውን ለውይይት እንዲያቀርቡ እና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ አስችለዋል፡፡

ሰብአዊ መብቶች፣ግብረ-ገብ ትምህርት እና አሳታፊ የመማር ማስተማር ዘዴን በተመለከተ የግብረ-ገብ መምህራን ስልጠና

ኢሰመኮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለተወጣጡ 84 የግብረ-ገብ ትምህርት መምህራን እና የትምህርት ባለሙያዎች ከጥቅምት 10 – 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል

የሰብአዊ መብቶች ትምህርትን በትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንዲጠናከር በትብብር ለመሥራት በኢሰመኮ እና በትምህርት ሚኒስቴር መካከል በ2015 ዓ.ም. የተፈረመውን የመግባቢያ ሰነድ እና ተከታዩን የትግበራ መርኃ ግብር መሠረት በማድረግ ኢሰመኮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለተወጣጡ 84 የግብረ-ገብ ትምህርት መምህራን እና የትምህርት ባለሙያዎች ከጥቅምት 10 – 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ በሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና በግብረ-ገብ ትምህርት መካከል ስላለ ቁርኝት፤ መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች ፅንሰ ሐሳብን እና አሳታፊ የመማር ማስተማር ዘዴዎችን ለግብረ-ገብ ትምህርት መጠቀም የሚኖረውን ጠቀሜታ በተመለከተ ሰፊ ዳሰሳ የተደረገ ሲሆን ተሳታፊዎቹ ለሰብአዊ መብቶች ትምህርት መጠናከር እና አሳታፊ የመማር ማስተማር ዘዴዎችን ለመተግበር እንዲሁም ለማስፋፋት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ለማድረግ ተነሳሽነት አሳድረዋል፡፡

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በስልጠናዎቹ ማጠቃለያ ለሰብአዊ መብቶች ትምህርት ተመራጭ የሆነውን አሳታፊ የመማር ማስተማር ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ ስለሚኖረው ጠቀሜታ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡