በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የተመራ የባለሙያዎች ቡድን ከነሐሴ 30 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በሐረሪ እና ሶማሊ ክልሎች የሥራ ጉብኝት አድርጓል፡፡ የሥራ ጉብኝቱ በተለይ ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች እና ማረሚያ ቤቶች የተጠርጣሪዎች እና የታራሚዎች አያያዝ የተመለከቱ ግኝቶች ላይ ያተኮረ ውይይት የተደረገበት ነው፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የተመራ የባለሙያዎች ቡድን በሐረሪ እና ሶማሊ ክልሎች የሥራ ጉብኝት አድርጓል

በሁለቱም ክልሎች በተደረጉ ውይይቶች የክልሎቹ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት፣ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ኮሚሽን፣ የፖሊስ ኮሚሽን፣ የሰላም እና ጸጥታ ቢሮ፣ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ተወካዮች ተገኝተዋል። በተለይም በክልሉ ፖሊስ ጣቢያዎች የተጠርጣሪዎች አያያዝ በኮሚሽኑ ክትትል የተለዩ ክፍተቶችን በተመለከተ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።

ጳጉሜን 1 ቀን 2015 ዓ.ም. በሶማሊ ክልል ጅግጅጋ ከተማ የክልሉ ፕሬዝዳንት ክቡር ሙስጠፋ መሀመድ በተገኙበት የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ሰፊ እና ውጤታማ ውይይት ተደርጓል። የክልሉ ፕሬዝዳንት በክልሉ የተሻለ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ እንዲኖር ለማድረግ ከኮሚሽኑ ጋር በተሻለ ሁኔታ በቅንጅት መሥራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ረገድ ሁሉም የክልሉ ተቋማት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የተመራ የባለሙያዎች ቡድን በሐረሪ እና ሶማሊ ክልሎች የሥራ ጉብኝት አድርጓል

የባለሙያዎች ቡድኑ በጅግጅጋ ከተማ የፋፈን ዞን ፖሊስ ጣቢያ እና የአለሙዲን ማረሚያ ቤትን የጎበኝ ሲሆን፣ በፖሊስ ጣቢያዎች ላይ የተስተዋሉ ውስንነቶች እንዲሻሻሉ ኮሚሽኑ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል። 

በሐረሪ ክልል የኢሰመኮ የባለሙያዎች ቡድን የሐረሪ ክልል ማረሚያ ቤት እና በሐረር ከተማ የጄኔላ ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ በመገኘት የታራሚዎች እና የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ምልከታ አድርጓል። ኢሰመኮ በክልሉ በፖሊስ ጣቢያዎች የተጠርጣሪዎች አያያዝ ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶች እንዲሻሻሉ ለክልሉ መንግሥት ዝርዝር ምክረ ሐሳብ ያቀረበ ሲሆን ለሰብአዊ መብቶች ሁኔታ መሻሻል በቅንጅት ለመሥራት መግባባት ላይ ተደርሷል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የተመራ የባለሙያዎች ቡድን በሐረሪ እና ሶማሊ ክልሎች የሥራ ጉብኝት አድርጓል

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በክልሎቹ ያለውን የሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ በተመለከት አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው “በተለያዩ ዘርፎች የአስተዳደር፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታን ለማሻሻል የሚሠሩ ሥራዎች ዋና ግባቸው ሰብአዊ መብቶችን ለማረጋገጥ መሆን እንዳለበት ጠቅሰው፤ ባለድርሻ አካላት በዚሁ እሳቤ ለሰብአዊ መብቶች መጠበቅ፣ መከበር እና መሟላት በከፍተኛ ቁርጠኝነት ከኢሰመኮ ጋር በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል” ብለዋል፡፡