የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአምስት ክልሎች እና በሁለት የከተማ አስተዳድሮች በሚገኙ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ ያሉ ሕፃናት የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን የተመለከተ ባለ 45 ገጽ የክትትል ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርጓል። ኮሚሽኑ በአማራ፣ በሐረሪ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በሲዳማ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ 25 የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ላይ ከመጋቢት 11 እስከ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል አከናውኗል።

በክትትሉ በአጠቃላይ ከ394 ሰዎች ጋር ቃለ መጠይቅ ተደርጓል፤ ከእነዚህም መካከል 250 ሕፃናት፣ 23 የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እና 121 የማሳደጊያ ተቋማት ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በቃለ መጠይቁ ተሳትፈዋል። ኮሚሽኑ 25 የቡድን ውይይቶችን በማሳደጊያ ተቋማት ከሚኖሩ ሕፃናት ጋር እና 17 የቡድን ውይይቶችን ደግሞ ከተቋማቱ ሠራተኞች ጋር በአጠቃላይ 42 የቡድን ውይይቶችን አከናውኗል። የአካል ምልከታም በየተቋማቱ በማድረግ እና ጠቃሚ ሰነዶችን በመመርመር መረጃ እና ማስረጃዎች ተሰብስቧል። በሪፖርቱ የክትትሉ ግኝቶች፣ መልካም ተሞክሮዎች እንዲሁም በማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ ለሕፃናት የሚሰጡ አገልግሎቶችን እና ጥበቃዎችን ለማሻሻል የሚያስችሉ ዝርዝር ምክረ ሐሳቦች ቀርበዋል።

ኮሚሽኑ ባከናወነው ክትትል የማሳደጊያ ተቋማቱን የቅበላ መስፈርቶች፣ አማራጭ የእንክብካቤና የድጋፍ አግልግሎቶች፣ የመረጃ አያያዝ፣ የሞግዚቶችና ሕፃናት ምጣኔ፣ ሕፃናቱ ከተቋማቱ የሚወጡበት ሂደት፣ የሕፃናቱ ከጥቃት የመጠበቅ ሁኔታ፣ የሕፃናቱ የተሳትፎ አደረጃጀቶች፣ ትምህርትን ጨምሮ ሌሎች መሠረታዊ አገልግሎቶችን የማግኘት እንዲሁም የአካል ጉዳተኛ ሕፃናት አያያዝን በተመለከተ ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) አማራጭ የሕፃናት እንክብካቤ መመሪያ እና የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ካወጣው የማኅበረሰብ አቀፍ የሕፃናት እንክብካቤ፣ መልሶ ማቀላቀልና ማዋሃድ፣ የአደራ ቤተሰብ፣ ጉዲፈቻና የተቋማዊ ክብካቤ አገልግሎት መመሪያ አንጻር ተገምግመዋል።

የጥራት ደረጃው እንደ ማሳደጊያ ተቋማቶቹ ዐቅም፣ የሕፃናት ዕድሜ እና ተቋማቶቹ እንደሚያቀርቡት የድጋፍ ዐይነት ቢለያይም ሁሉም ማሳደጊያ ተቋማት የምግብ፣ የንጹሕ መጠጥ ውሃ፣ የመጠለያ፣ የአልባሳት፣ የግል እና የጋራ ንጽሕና መጠበቂያ ግብአቶች እንዲሁም የጤና፣ የትምህርት፣ የጨዋታ እና መዝናኛ አግልግሎቶችን ማቅረባቸው በመልካም እመርታነት በሪፖርቱ ተገልጿል።

የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማቱ በተሟላ መልኩ የሕፃናቱን ሁኔታ መሠረት በማድረግ የተሰባጠረ እና ዝርዝር መረጃ እንዳልያዙ፣ ከሁለት ተቋማት በስተቀር በሁሉም ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ለተለያዩ ጥቃቶች የተጋለጡ መሆናቸው፣ የሕፃናት ምግብ የማግኘት መብት በአቅርቦት፣ በጥራትና በተስማሚነት እንዲሁም ከምግብ ሥርዓት ተገቢነት አንጻር የተሟላ እንዳልሆነ፤ በአንድ ክፍል ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕፃናት መኖራቸው እና በአብዛኞቹ ተቋማት ሕፃናቱ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችል እንዲሁም ወጥና ለሕፃናት ምቹ (child friendly) የሆነ የቅሬታ መቀበያ እና መፍቻ ሥርዓት በተሟላ ሁኔታ አለመኖሩ በክትትሉ ከተለዩ ዋና ዋና የመብት ጥሰቶች መካከል ናቸው። በተጨማሪም ክትትል የተደረገባቸው አብዛኛዎቹ የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት የአካል ጉዳተኛ ሕፃናትን የአካል ጉዳት ዐይነት እና ፍላጎት መሠረት ያደረግ አገልግሎትን ከማቅረብ አንጻር ክፍተት እንዳለባቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ መንግሥት ከቤተሰብ እንክብካቤ ውጪ በማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ ለሚያድጉ ሕፃናት የሚሰጡትን አገልግሎቶች እና እንክብካቤዎች ከመደገፍ በተጨማሪ የሕፃናትን ሰብአዊ መብቶች ከማክበር፣ ከመጠበቅ እና ከማሟላት አንጻር አገልግሎቶቹ እና እንክብካቤዎቹ በሕፃናት

መብቶች የተቃኙ መሆናቸውን በየጊዜው በመከታተል እና በመፈተሽ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል፡፡