የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሕፃናት በቂ የኑሮ ደረጃ የማግኘት መብት ጋር የተያያዙ ሀገራዊ ሕጎች እና ፖሊሲዎች ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ጋር መጣጣማቸውን ለመፈተሽ ባከናወነው የሕግ ዳሰሳ ጥናት ግኝቶች ላይ ከመጋቢት 21 እስከ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በባሕር ዳር ከተማ ዐውደ ጥናት አካሂዷል፡፡

ዐውደ-ጥናቱ በሕግ ዳሰሳ ጥናት የተለዩ ግኝቶች ላይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ለመመካከር እና አግባብነት ያላቸውን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ያለመ ሲሆን ከፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ከአማራ፣ከኦሮሚያ እና ከደቡብ ክልሎች የተውጣጡ የተለያዩ ቢሮዎች ተወካዮችን ጨምሮ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፈዋል።

በዐውደ-ጥናቱ ከሕፃናት በቂ የኑሮ ደረጃ የማግኘት መብት ጋር የተያያዙ ዋና ዋና ሀገራዊ የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፎች ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ጋር ያላቸው አግባብነት እና ክፍተቶች ቀርበዋል። በቂ የኑሮ ደረጃ የማግኘት መብት ለሕፃናት አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ መንፈሳዊ፣ ሞራላዊና ማኅበራዊ እድገት አስፈላጊ የሆኑ በቂ ምግብ፣ አልባሳት፣ የመኖሪያ ቤት፣ የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ጨምሮ ቀጣይነት ያለው የኑሮ ሁኔታን የሚያሻሽሉ እርምጃዎችን የሚመለከት ስለመሆኑ ተገልጿል። ወላጆች እና ሕጋዊ አሳዳጊዎች ያለባቸውን ግዴታዎች፣ መንግሥት እንደ ሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ እና ዐቅም ሊወስድ ስለሚገባቸው ተገቢ እርምጃዎች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሕፃናትን በቂ የኑሮ ደረጃ የማግኘት መብት ሁኔታ እንዲሻሻል ስላለባቸው ኃላፊነት በዝርዝር ውይይት ተደርጓል፡፡

የዐውደ-ጥናቱ ተሳታፊዎች በሕፃናት በቂ የኑሮ ደረጃ የማግኘት መብትን እንዲሁም የሕግ እና የፖሊሲ ክፍተቶች ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ መጨበጣቸውን፣ መብቱን ለማስከበር በግልና ባላቸው የኃላፊነት ደረጃ እንደሚሠሩ፣ በሕግ እና በፖሊሲ ክፍተቶች ዙሪያ የተሰጡትን ምክረ ሐሳቦች በተመለከተ የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ ለማስቻልና ለተፈጻሚነታቸውም ግፊት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

በዐውደ-ጥናቱ የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ኮሚሽኑ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ከተካተቱ መብቶች መካከል የሕፃናት በቂ የኑሮ ደረጃ የማግኘት መብት ላይ ያከናወነው የሕግ እና የፖሊሲ ግምገማ ጥናት የክትትል ሥራዎችን ለማከናወን፣ የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ለመቅረጽ እንዲሁም የባለግዴታዎችን እና ባለሙያዎችን ዐቅም እና ግንዛቤ ለማጎልበት ፋይዳው ከፍ ያለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡