የባለሞያ አስተያየት ከኢሰመኮ
አረጋ ሻረው
የሰብአዊ መብቶች ባለሙያ
የአካል ጉዳተኞችና አረጋውያን ሥራ ክፍል

ሠራተኞች በሥራ ላይ በሚደርስ አደጋ ወይም በሥራ ምክንያት በሚመጣ በሽታ ለአካል ጉዳት ይዳረጋሉ። የአካል ጉዳት የመሥራት ችሎታ መቀነስን ወይም ማጣትን በሚያስከትል ሁኔታ በሥራ ላይ የሚደርስ ጉዳት ሲሆን፣  ጊዜያዊ የአካል ጉዳት፣ ዘላቂ ከፊል የአካል ጉዳት፣ ዘላቂ ሙሉ የአካል ጉዳት ወይም ሞት ሊያስከትል ይችላል። እ.ኤ.አ. ከ2020 እስከ 2022 በሚሸፍነው የዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት የማኅበራዊ ዋስትና ሪፖርት መሠረት በዓለም ላይ በየዓመቱ 374 ሚሊዮን ሠራተኞች የሥራ ላይ ጉዳት ይደርስባቸዋል፡፡ ሆኖም የሥራ ላይ ጉዳት ዋስትና ሽፋን ያላቸው 35.4% ሠራተኞች ብቻ ሲሆኑ፣ ምጣኔው በአፍሪካ ደረጃ ወደ 18.4%፣ ከሰሀራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ ወደ 14.8% ዝቅ ይላል። የሥራ ላይ አካል ጉዳት የሠራተኞችን የመሥራት ችሎታ በተለያየ ደረጃ በመጉዳት ወይም በማሳጣት የሥራ ውል መቋረጥን ሊያስከትል ወይም በተለያየ መልኩ የሥራ ዋስትናን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል። በሥራ ላይ አካል ጉዳት ሥራቸውን የሚያጡ ሰዎች ጥገኝነት፣ ሥነ-ልቦናዊ ጉዳት እና ሌሎች ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎች ያጋጥሟቸዋል።

ደኅንነቱ የተጠበቀ የሥራ አካባቢ እና የሥራ ዋስትና የማግኘት መብቶች በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና ብሔራዊ ሕጎች ዕውቅና እና ጥበቃ የሚደረግላቸው የሠራተኞች መሠረታዊ መብቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት መሠረት መንግሥት የሠራተኞችን ጤንነት፣ ደኅንነትና የኑሮ ደረጃ ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ ያለበት ሲሆን፣ ሠራተኞችም ጤናማ እና አደጋ የማያደርስ የሥራ አካባቢ የማግኘት መብት አላቸው። የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትን የሚገዙ ሌሎች ብሔራዊ ሕጎች ሠራተኞች ደኅንነቱና ጤንነቱ በተጠበቀ የሥራ አካባቢ እንዲሠሩ ከመደንገግ ባሻገር፣ በሥራ ምክንያት ለሚደርስ የአካል ጉዳት እንደነገሩ ሁኔታ ተገቢውን ሕክምና፣ በየጊዜው የሚደረግ የጉዳት ክፍያ እንዲሁም የጉዳት ጡረታ ወይም ዳረጎት ወይም ካሣ የማግኘት መብት እንዳላቸው እና በሞት ጊዜም ጥገኞች የዚህ መብት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይደነግጋሉ።

የሥራ ላይ አካል ጉዳት ደርሶባቸው የሥራ ችሎታቸውን ወይም ሥራቸውን ያጡ ሰዎች ማኅበራዊ ዋስትና እና መድን፣ የመልሶ ማቋቋምና ተሐድሶ ድጋፍ እንዲሁም ጉዳታቸውን እና ችሎታቸውን ያገናዘበ ሥራ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል። ይህም በሥራ ላይ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በሥራ ላይ ለማቆየትና ወደ ሥራ ለመመለስ እንዲችሉ ድጋፍ ማድረግን የሚጨምር ሲሆን ለአካል ጉዳተኞች የሥራ ዋስትና መብትን ማረጋገጥ ብሎም በሁሉም የሕይወት ገጽታዎች ውስጥ የተሟላ ተካታችነትና ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ ነው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ሀገራት የሥራ ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን ሠራተኞች የጉዳት ጡረታ አበል ተጠቃሚ የማድረግ ዓላማ ያለው የሥራ ዋስትና መርኃ ግብር ይከተሉ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ጉዳት የደረሰባቸውን ሠራተኞች መልሶ በማቋቋም እና ወደ ሥራ በመመለስ ላይ ትኩረት ማድረግን መርጠዋል። ይህም ወጪ ከመቆጠብ ባሻገር የሥራ ላይ አካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የሥራ መብት እንዲከበር፣ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ እና ማኅበራዊ ተቀባይነት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በዚህ ረገድ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ጉዳት የደረሰባቸውን ሠራተኞች ወደ ሥራ ሊመልስ በሚችል የሙያ ስልጠና ላይ ትኩረት የሚያደርግ የሕግ ማዕቀፍ፣ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ አላቸው፡፡ በተለይ ጀርመን ከጉዳት ጡረታ በፊት መልሶ ማገገምን የሚያስቀድም መርሕ ትከተላለች። አውስትራሊያ፣ ማሌዥያ፣ ታንዛንያ ወዘተ. የሥራ ላይ አካል ጉዳት ያጋጠማቸውን ሰዎች ወደ ቀድሞ ሥራቸው ሊመልስ በሚችል የመልሶ ማቋቋም እና የሙያ ስልጠናዎች ሥራ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።

በኢትዮጵያ በሥራ ላይ በሚደርስ አደጋ ወይም በሥራ ምክንያት በሚመጣ በሽታ ሠራተኞች ለአካል ጉዳት ተዳርገው ከሥራ መሰናበት ይገጥማቸዋል፡፡ በተለያዩ ብሔራዊ ሕጎች ውስጥ በሥራ ላይ ለሚደርስ የአካል ጉዳት ተገቢውን ሕክምና፣ በየጊዜው የሚደረግ የጉዳት ክፍያ እንዲሁም የጉዳት ጡረታ ወይም ዳረጎት ወይም ካሣ የማግኘት መብት ዕውቅና ማግኘቱ አበረታች እርምጃ ቢሆንም፣ አሠሪዎች የተለያዩ የሥራ ላይ ማስተካከያዎችን በማድረግ ጉዳት የደረሰባቸውን ሠራተኞች በሥራ ላይ እንዲቆዩ ከማድረግ ይልቅ ከሥራ ማሰናበትን ይመርጣሉ። በሕግ እና በፖሊሲ ደረጃ  የሥራ ላይ አካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች በነበሩበት የሥራ መስክ ላይ እንዲቆዩ ወይም ወደ ሥራ እንዲመለሱ ለማድረግ የሚያስችል የሙያ ማገገሚያ (Vocational Rehablitation) እና የሙያ ክኅሎት ስልጠና (Vocational Skills Training) መርኃ ግብር አለመቀረጹ ለዚህ ተግባር በር ከፍቷል።

በመሆኑም መንግሥት የሥራ ላይ ጉዳት የገጠማቸውን ሠራተኞች የሥራ ዋስትና መብት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የሕግ፣ የፖሊሲ እና የአሠራር ማሻሻያዎችን ማድረግ እንዲሁም በተደረጉ ማሻሻያዎች ላይ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ማዘጋጀት እና ማስተዋወቅ አለበት፡፡ የሚደረጉት ማሻሻያዎችም ሠራተኞች በሥራ ላይ ጉዳት በሚገጥማቸው ወቅት በነበሩበት መሥሪያ ቤት፣ በያዙት የሥራ መደብ ወይም ሌላ የሥራ መደብ ላይ ለመቆየት (job retention) ወይም በአዲስ መልኩ ወደ ሥራ ለመመለስ (return to work የሚያስችሉ የማቋቋምና የተሐድሶ አገልግሎቶችን ሊያካትት ይገባል፡፡ በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎች ሠራተኞች የገጠማቸውን የጉዳት ዐይነትና መጠን ከግምት በማስገባት ያለምንም ለውጥ በፊት ወደ ነበሩበት ቦታ መመለስ ወይም ሥራውን እና የሥራ ቦታውን በማስተካከል ወደ ሥራ ቦታቸው መመለስ ወይም ወደ ሌላ የሥራ መደብ ማዛወር ሊሆን ይችላል፡፡ በተጨማሪ በሥራ ላይ ጉዳት የገጠማቸው ሠራተኞች አስቸኳይ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ የማገገሚያ ድጋፍ አገልግሎት የሚያገኙበትን እና ቀስ በቀስ ወደ ሥራ የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት፤ ከሥራው ባህሪ አንጻር በነበሩበት የሥራ መደብ መቆየት የማይችሉ መሆኑ ሲረጋገጥ ደግሞ ከሠራተኞቹ ጋር በመወያየት አማራጭ የሥራ ዘርፎችን ማመቻቸት፤ የሠራተኞችን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ የተለያዩ ድጋፎችና ተመጣጣኝ ማመቻቸቶችን ማቅረብ፤ የሙያና የሥራ ላይ ስልጠናዎች ማዘጋጀት፤ የድጋፍ መሣሪያዎች ማቅረብ፤ የሥራ መሣሪያዎችን ማስተካከልና ምቹ ማድረግ፤  ተደራሽ የሥራ ቦታ መፍጠር፤ የሥራ ሰዓት ለውጥ ማድረግ እንዲሁም ሌሎች ተገቢ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል የሕግና ፖሊሲ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እና አተገባበሩን በቋሚነት መከታተል ይገባል። ማዕቀፉ መደበኛ ባልሆኑ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ሠራተኞችን ጨምሮ ሁሉንም ዐይነት ሠራተኞች ያካተተ እና ኢትዮጵያ በአካል ጉዳተኞች መብቶች ስምምነት የገባችውን የአካል ጉዳት የገጠማቸውን ሠራተኞች መልሶ የማቋቋም፣ የተሐድሶ አገልግሎት የመስጠት እና ወደ ሥራ የመመለስ ግዴታ ለመወጣት የሚያስችሉ እርምጃዎችን የያዘ መሆን አለበት። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ የሥራ ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን ሠራተኞች መብት ለማስከበር የሚረዱ ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት ያወጣቸውን የማኅበራዊ ዋስትና ስምምነት (Social Security (Minimum Standard) Convention, 1952 No. 102) እና የሥራ ላይ ጉዳት ክፍያ ስምምነት (Employment Injury Benefits Convention, 1964, No.121) በማጽደቅ የሀገሪቱ የሕግ አካል ልታደርግ ይገባል፡፡