የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከጥር እስከ መጋቢት ወር 2016 ዓ.ም. ባሉት ሦስት ወራት በሽግግር ፍትሕ እና በሰብአዊ መብቶች ፅንሰ ሐሳብ ዙሪያ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ለሚገኙ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች፤ ለወጣቶች ማኅበራት አባላት እና አመራሮች እንዲሁም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የሰላም ፎረም እና የተማሪ መማክርት አባላት ስልጠናዎችን ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም የሥነ/ኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና ማስፋፋት ላይ የሚኖራቸውን አስተዋጽዖ ለማሳደግ ያለመ የሰብአዊ መብቶች ስልጠና እንዲሁም የተጠርጣሪዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝን አስመልክቶ ለፖሊስ አባላት ስልጠናዎችን ሰጥቷል።

ኢሰመኮ በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ላይ አምስት የስልጠና መድረኮችን በአርባ ምንጭ፣ በጋምቤላ፣ በሃዋሳ፣ በሆሳዕና እና በጅማ ከተሞች በማዘጋጀት በአጠቃላይ ለ159 የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል። በስልጠናው ከሰብአዊ መብቶች እና ከሽግግር ፍትሕ ፅንሰ ሐሳብ በተጨማሪ በተለያዩ ሀገራት በግጭት ወቅት እንዲሁም በሽግግር ፍትሕ ሂደት የሃይማኖት መሪዎች እና የሀገር ሽማግሌዎች ስለነበራቸው ተሳትፎና ተሞክሮ ቀርቧል። በዚህም በኢትዮጵያ ሊተገበር በታቀደው የሽግግር ፍትሕ ሂደትም ውስጥ ሰልጣኞቹ ሊኖራቸው የሚችለውን ሚና ማስገንዘብ ተችሏል፡፡

ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ፅንሰ ሐሳብ እና የሽግግር ፍትሕ ምንነት፣ ዓላማ እና አላባውያንን የተመለከተና በሂደቱ የወጣቶችን ተሳትፎ ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ ክህሎቶችን የሚያለማምድ የአሰልጣኞች ስልጠና ከጥር 20 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ ለ34 ተሳታፊዎች እንዲሁም ከመጋቢት 23 እስከ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. ለ35 ወጣቶች በሆሳዕና ከተማ ሰጥቷል፡፡ በስልጠናዎቹ ላይ የወጣቶች ማኅበራት፣ የዩኒቨርሲቲ የሰላም ፎረም እና የተማሪ መማክርት አመራሮች እና አባላት ተሳትፈዋል፡፡ ከእነዚህ ስልጠናዎች በተጨማሪ በሁለተኛው ሩብ ዓመት የተሰጠውን የሽግግር ፍትሕ እና የሰብአዊ መብቶች ስልጠና የወሰዱ ወጣቶች ስልጠናውን መሠረት አድርገው በአዳማ፣ በሃዋሳ እና በመቀሌ ከተሞች ባካሄዷቸው የስልጠና መድረኮች በድምሩ 122 ወጣቶችን አሰልጥነዋል። በእነዚህም ስልጠናዎች ተሳታፊዎች ለሰብአዊ መብቶች መከበር በግለሰብ ደረጃም ይሁን በየማኅበራቸው በሽግግር ፍትሕ ሂደት ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ግንዛቤ አግኝተዋል፡፡

ኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶችን ግንዛቤ በማኅበረሰብ ውስጥ ለማስፋፋት ለሚያደርገው ጥረት አጋዥ መንገዶች አንዱ የሥነ/ኪነ-ጥበብ ሥራዎችን መጠቀም በመሆኑ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ስለ ሰብአዊ መብቶች ፅንሰ ሐሳብ ለማስገንዘብ የሚያስችል ስልጠና ከጥር 28 እስከ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ከተለያዩ የቴአትርና ጥበባት ማኅበራት ለተውጣጡ 26 ተሳታፊዎች ሰጥቷል፡፡ በዚህ ስልጠና በተለይም ስለ ሴቶች፣ ሕፃናት እና ሥነ/ኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ሰብአዊ መብቶች ትኩረት ተሰጥቷል። ከስልጠናው በኋላ ተሳታፊዎች በሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እና ግንዛቤ ዙሪያ በሙያቸው ሊያበረክቱ የሚችሉትን አስተዋጽዖ አስመልክቶ የድርጊት መርኃ ግብር እንዲያዘጋጁ የተደረገ ሲሆን ተግባራዊነቱን ለማረጋገጥ ሙያዊ እገዛ እንዲደረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ኢሰመኮ ፖሊሶች ከሥራቸው ጋር ተዛማጅ ስለሆኑ የሰብአዊ መብቶች ዕሴቶች ምንነት እና ተግባራዊነት፣ ስለተጠርጣሪዎች መብቶች እና የፖሊስ ተጠያቂነትን በተመለከተ ዕውቀታቸውን፣ አመለካከታቸውን እና ክህሎታቸውን ለመገንባት ያለመ ስልጠና ከመጋቢት 25 እስከ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ሰጥቷል፡፡ በስልጠናው በሸገር ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ 35 የፖሊስ አባላትና አመራሮች ተሳተፊ ሆነዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ ፖሊስ የሰዎችን መብቶች እና ነጻነት በመጠበቅ፣ የሕዝብን ሰላምና ጸጥታ በማስከበር እንዲሁም የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው በመረዳት ተጠርጣሪዎችን በሚይዙበትና በቁጥጥር ሥር በሚያውሉበት እንዲሁም የወንጀል ምርመራ በሚያደርጉበት ጊዜ ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚገቡ መሠረታዊ የሰብአዊ መብቶች መመዘኛዎች ላይ ግንዛቤያቸውን እንዲያዳብሩ ተደርጓል፡፡

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር መቅደስ ታደለ ሥልጠናዎቹን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክት “ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት መሪዎች በሰብአዊ መብቶች እና በሽግግር ፍትሕ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ማዳበር ወደፊት በሀገራችን ተግባራዊ በሚደረገው የሽግግር ፍትሕ ሂደት ላይ የሚጠበቅባቸውን አወንታዊ ሚና እንዲጫወቱ ያግዛል” ብለዋል።