የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሰባት ክልሎች በሰፋፊ እርሻ ልማት ጣቢያዎች ውስጥ የሚሠሩ ሴቶች እና ወጣት ሠራተኞች የሰብአዊ መብቶች ሁኔታን አስመልክቶ ባከናወነው ክትትል በተለዩ ግኝቶች እና በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ ከአራት ክልሎች ከተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ጥቅምት 28 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የጋምቤላ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና የአፋር ክልሎች እንዲሁም የዞኖች ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ፣ የሥራና ክህሎት፣ የጤና እና የኢንቨስትመንት ቢሮዎች፤ የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና የእርሻ ልማት ጣቢያዎች ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ከሴቶች እና ከወጣት ሠራተኞች መብቶች ጋር በተያያዘ ያሉ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች የሕግ ማዕቀፎች ለውይይት መነሻ ቀርበዋል። ከሠራተኞች የእረፍት ፈቃድ እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ፣ በተገደበ ሰዓት ውስጥ ከመሥራት፣ ከሠራተኞች መሠረታዊ ፍላጎቶች፣ ጤናማ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የሥራ ሁኔታ፣ ለተመሳሳይ ሥራ ተመሳሳይ ክፍያ እና በቂ ደመወዝ ከማግኘት፣ ከወሲባዊ ትንኮሳና ጥቃት ከመጠበቅ መብት እና ከሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ አንጻር በክትትሉ የተለዩ ግኝቶች፣ አሳሳቢ ሁኔታዎች እና የተሰጡ ምክረ ሐሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢሰመኮ ባካሄደው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል የተለዩት ግኝቶች በእርሻ ልማት ጣቢያዎች በሚገኙ ሴቶች እና ወጣት ሠራተኞች ላይ የሚፈጸሙትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አጉልተው ያሳዩ መሆናቸውን ጠቅሰው የእርሻ ልማት ጣቢያዎች በሥራቸው ያሉ ሠራተኞችን ሰብአዊ መብቶች ለማስከበር እና በቀጣይ የቅድመ መከላከል ሥራዎችን ለማከናወን መነሻ እንደሚሆናቸው ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ኢሰመኮ ግኝቶቹን እና ምክረ ሐሳቦቹን በጽሑፍ ለእርሻ ልማት ጣቢያዎቹ እና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ካሳወቀ በኋላ ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ የድርጊት መርኃ ግብር አዘጋጅተው ለኮሚሽኑ እንደሚልኩ እና ተግባራዊ ማድረግ እንደሚጀምሩ ተስማምተዋል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ የእርሻ ልማት ጣቢያዎች የሠራተኞቻቸውን በተለይም የሴቶች እና የወጣት ሠራተኞችን ሰብአዊ መብቶች ከማስጠበቅ አንጻር ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም በእርሻ ልማት ጣቢያዎቹ የሚስተዋሉ ከ15 ዓመት በታች ያሉ ሕፃናትን ቀጥሮ ማሠራት፣ ለጾታዊ ጥቃት አጋላጭ የሆኑ ሁኔታዎች እና አካላዊ ጉዳቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮች ጊዜ የማይሰጡና አሳሳቢ በመሆናቸው በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጥሪ አቅርበዋል። በተጨማሪም በእርሻ ልማት ጣቢያዎች ውስጥ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ለማስቆም እና ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ እንዲሠሩ አሳስበዋል።