የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2015 ዓ.ም. በሴቶች እና በሕፃናት መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት የተነሱ የሴቶች መብቶች ጉዳዮችን መሠረት ያደረገ የውይይት መድረክ ከማኅበራዊ ሚዲያና ከኪነጥበብ ይዘት ፈጣሪዎች እንዲሁም በሴቶች መብቶች ላይ ከሚሠሩ ሲቪል ማኅበራት ጋር ታኅሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አካሄደ።

የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች

የውይይቱ ዐላማ ባለመብቶች የዓመታዊ የዘርፍ ሪፖርቱን ግኝቶችና ምክረ ሐሳቦች እንዲያውቋቸውና በሚሠሩዋቸው የውትወታ ሥራዎች እንደግብአት እንዲጠቀሙባቸው ማድረግ ነው። በመድረኩ በ2015 ዓ.ም. ኢሰመኮ በለያቸው የሴቶች ሰብአዊ መብቶች ሁኔታዎች ላይ የታዩ እመርታዎች እንዲሁም አሳሳቢ ሁኔታዎች የቀረቡ ሲሆን፣ በተለይ የሴቶች ከጥቃት የመጠበቅ መብት፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር የጥቃት ተጎጂ ሴቶች መብቶች አያያዝ፣ የሴቶች የጤናማ የሥራ ሁኔታ መብት፣ የፖለቲካ ተሳትፎ መብት እና የሴቶች የሰላምና ደኅንነት መብቶች ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸው ተገልጿል።

የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ

የማኅበራዊ ሚዲያና የኪነጥበብ ይዘት ፈጣሪዎች እንዲሁም የሲቪል ማኅበራት እነዚህን መረጃዎች ተጠቅመው ግንዛቤ በማስጨበጥና ውትወታ በማድረግ ለሴቶች ሰብአዊ መብቶች መጠበቅ እና መስፋፋት የራሳቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ፤ ይህንንም ለማድረግ ያግዛቸው ዘንድ መከተል ስላለባቸው የሰብአዊ መብቶች መርሖች አጭር ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የምክክሩ ተሳታፊዎች የሴቶችን መብቶች የተመለከቱ ሥራዎች ዘርፈ ብዙ ሙያዎችን ቢያካትቱ እና የተለያዩ ዐውዶችን ከግንዛቤ ቢያስገቡ ይበልጥ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል። አያይዘውም እንደዚህ ዐይነት ሲቪል ማኅበራት እና የማኅበራዊ ሚዲያ እንዲሁም የኪነጥበብ ይዘት ፈጣሪዎች ተቀናጅተው የሚሠሩበትን ዕድል የሚሰጥ መድረክ መዘጋጀቱ እንዲቀጥል ሐሳብ አቅርበዋል።

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ

የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ “የሴቶች መብቶችን ለማስጠበቅ እና ለማስፋፋት በሚሠሩ ሥራዎች አጋርነት መፍጠርና የሰብአዊ መብቶች መርሖችን ማእከል ያደረገ ቀጣይነት ያለው ንቅናቄ ያስፈልጋል” ብለዋል። የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ በበኩላቸው “ሴቶች ብዝኅነት ያላቸው የመብት ፍላጎቶቻቸውን ለማስጠበቅ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን የሚጠይቅ እና አንድ መፍትሔ ያለው ባለመሆኑ በሁሉም መስክ ሰብአዊ መብቶችን ማእከል ያደረገ ንቅናቄ ሊደረግ ይገባል” ሲሉ ገልጸዋል።