የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ስር በሚገኙ ወረዳና ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጣቢያዎች በ2014 ዓ.ም. 4ኛ ሩብ ዓመት እና በ2015 ዓ.ም. 1ኛ ሩብ ዓመት ውስጥ የተጠርጣሪዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ባደረገው ክትትል የተለዩ ግኝቶችንና የተሰጡ ምክረ-ሃሳቦች አፈጻጸም ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ከኅዳር 8 እስከ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በመተከል ዞን ፓዌ ከተማ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩም የመተከል ዞን ፍትሕ መምሪያ ኃላፊ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የመተከል ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ፣ የመተከል ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፤ ከወረዳዎች ፖሊስ ጽሕፈት ቤቶች የመጡ አዛዦችን እና የአቤቱታ መቀበልና መመርመር፤ የወንጀል ሥራ ሂደት አስተባባሪ እንዲሁም የሴቶችና የሕፃናት ባለሙያ ፖሊስ አባላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ለውይይት ከቀረቡት የክትትሉ ግኝቶች መካከል በፖሊስ ጣቢያዎች በተወሰኑ የሥነ-ምግባር ችግር ባለባቸው የፖሊስ አባላት በተጠርጣሪዎች ላይ የተፈጸሙ ድብደባዎች እና ኢሰብአዊ አያያዞችን ተከትሎ ጉዳት ስለመድረሱና የአጥፊዎች በሕግ አግባብ ተጠያቂነት መጓደል፣ መጥሪያ ሳይወጣ እንዲሁም በፍርድ ቤት የእስር መያዣ ትዕዛዝ ሳይሰጥ ሰዎችን በዘፈቀደ ይዞ ማሰር፣ ለእስር የሚያበቃ በቂ ምክንያት ሳይኖር ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ማቆየትና የተጠረጠሩበትን ምክንያት ወዲያው አለማሳወቅ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በተጨማሪም ተጠርጣሪዎች ምርመራ ሳይጀመርባቸውና ክስ ሳይመሰረትባቸው በጣቢያ ለወራት ማቆየት እንዲሁም ፍርድ ቤት በ48 ሰዓታት ውስጥ አለማቅረብ፣ ዋስትና በሚያስፈቅዱ ጉዳዮች በዋስ ያለመለቀቅ፣ አልፎ አልፎም በፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቅ የተፈቀደለትን ሰው የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ባለማክበር በእስር ማቆየት ፣ የፍትሐ ብሔር ግዴታዎችን ባልተወጡና በደንብ መተላለፍ የሚያስጠይቁ ጉዳዮችን ምክንያት አድርጎ ያለአግባብ እስር መፈጸም፣ ለሴት እና ወጣት ተጠርጣሪዎች ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ የሚደረግበት ሁኔታ በጣቢያዎች አለመኖር የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ የማቆያ ክፍሎች ጥበት እና የንጽሕና ጉድለት እንዲሁም ለእስረኞች በቂ የውሃ አቅርቦት አለመኖር ችግርና በሌላ በኩል ወጥነት የሌለው ዘመናዊ የተጠርጣሪዎች መረጃ አያያዝ አለመኖር ችግሮች በዋናነት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በመተከል ዞን ለረጅም ዓመታት ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ በኮማንድ ፖስት ስር በቆዩባቸው ጊዜያቶች የመብቶች ጥሰት በዜጎች ላይ እንደተፈጸመ በመጥቀስ አሁን የመጣውን አንጻራዊ ሰላም በመጠቀም የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብቶች የማስከበር ኃላፊነታቸውን በቅንጅት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢሰመኮ አሶሳ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጉርሜሳ በፉጣ በበኩላቸው በፖሊስ ጣቢያዎች በተደረገው ክትትል መሰረት በርካታ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ስለመኖሩ ግልጽ ጉዳይ ቢሆንም ኮሚሽኑ የሚሰጣቸውን ምክረ-ሃሳቦች ተቀብሎ በመፈጸም ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻሎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ አክለውም የፍትሕ አካሉ የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች በማክበር እና ማስከበር ዙሪያ ዋና ባለድርሻ በመሆኑ በተጠርጣሪዎች ላይ ድብደባና ኢሰብአዊ ድርጊቶችን የሚፈጽሙ የፀጥታ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡