የፌዴራል መንግሥት እና የክልል የፀጥታ ኃይሎች “በተቀናጀ መንገድ የሕግ በላይነትን ማስከበር” በሚል ባለፉት ጥቂት ቀናት መውሰድ በጀመሩት እርምጃ፣ ጋዜጠኞችና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ታስረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሁኔታዎችን በቅርበት እየተከታተለ ሲሆን፤ የተወሰኑት ተጠርጣሪ ታሳሪዎች በቤተሰቦቻቸው የተጎበኙና በተለያየ የጊዜ መጠን ወደ ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፤ በርካታ ታሳሪዎች ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ መታሰራቸውን፣ ፍርድ ቤት ያለመቅረባቸውን፣ በቤተሰብ አለመጎብኘታቸውን ተመልክቷል።  በተለይም በአማራ ክልል በርካታ ታሳሪዎች ከመደበኛ መኖሪያ አካባቢያቸውና ከመደበኛ እስር ቦታዎች ውጭ ጭምር በመታሰራቸው ቤተሰቦቻቸው ያሉበትን እንኳን ለማወቅ መቸገራቸውን ኮሚሽኑ ተረድቷል፡፡

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ሊወስድ የሚችላቸውን እርምጃዎች ኢሰመኮ ቢገነዘብም “የዚህ አይነት የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን ያልተከተለና የተስፋፋ እስር ተገቢ አለመሆኑን” የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ገልጸዋል። “በተለይም የፌደራልም ሆነ የክልል የፀጥታ ኃይሎች ተጠርጣሪዎችን ከወንጀል ምርመራ በፊት ከማሰር፣ ጋዜጠኞችን በስራቸው ምክንያት ከማሰር እና ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ሰዎችን ከማሰር ሊታቀቡ ይገባል። እንዲሁም በማናቸውም አይነት ሁኔታ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ ቤተሰቦቻቸው ወዲያውኑ እንዲያውቁ እንዲደረግና ወደ ፍርድ ቤትም ሊቀርቡ ይገባል” ብለዋል፡፡ ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም ኢሰመኮ በማናቸውም ስፍራ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ሁኔታ በድንገተኛ ጉብኝት ለመከታተል በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት፣ ክትትል በማድረግ ላይ ስለሆነ ሁሉም የፌደራል እና የክልል መንግሥታት አካላት ለኮሚሽኑ ሥራ የመተባበር ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡