የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ/ኮሚሽኑ) በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው የትጥቅ ግጭት ላስከተለው መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ዘላቂ እልባት ለመስጠት ሰላማዊ መፍትሔ ማፈላለግን ጨምሮ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል የሚያግዙ አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በተለያየ ጊዜ ባወጣቸው መግለጫዎች ማሳሳቡ ይታወሳል። ሆኖም በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በአጠቃላይ የግጭት ዐውድ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርስ ጉዳት፣ እንዲሁም በታጣቂ ቡድኖች በሚፈጸሙ ጥቃቶች ከሚደርሱ ጉዳቶች በተጨማሪ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ከሕግ ውጭ ግድያዎች አሁንም እጅግ አሳሳቢ እና እልባት ያላገኙ መሆናቸው እንደቀጠለ ነው። የትጥቅ ግጭቱ በሰብአዊ መብቶች እና በማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ እያስከተለ ያለውን ጉዳት/አሉታዊ ተጽእኖ ነዋሪዎችን፣ የዐይን እማኞችን፣ ተጎጂዎችን እና የተጎጂ ቤተሰቦችን እንዲሁም መንግሥትን በማነጋገር ኮሚሽኑ በቅርበት መከታተሉን ቀጥሏል።

በሰሜን ጎጃም ዞን በመራዊ ከተማ ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በታጠቁ ኃይሎች (በተለምዶ ፋኖ በመባል የሚጠሩት) መካከል ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ውጊያ መካሄዱን ተከትሎ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ ስለደረሰው ጉዳት ኢሰመኮ ምርመራ እያከናወነ ቢሆንም፤ ኮሚሽኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የጠየቃቸው መረጃዎች እና ምላሽ ገና ያልደረሰ በመሆኑና በጸጥታው ሁኔታና ልዩ ልዩ ተዛማጅ ምክንያቶች ሙሉ መረጃዎች ገና በተሟላ ሁኔታ ማሰባሰብ ባለመቻሉ የምርመራ ሥራው በተሟላ መልኩ ሊጠናቀቅ አልቻለም፡፡

የተሟላ ምርመራ መደረጉ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ኢሰመኮ እስከ አሁን ድረስ ባደረገው ክትትል ኮሚሽኑ ማንነታቸውን ማረጋገጥ የቻላቸውን ቢያንስ 45 ሲቪል ሰዎችን የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ምክንያት ከሕግ ውጭ መግደላቸውን፣ እንዲሁም “የፋኖ አባላት ናቸው” በሚል ተጠርጥረው የተያዙ እና ለጊዜው ብዛታቸውን ለማረጋገጥ ያልተቻለ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል። ኮሚሽኑ ከደረሱት በርካታ ጥቆማዎችና ከልዩ ልዩ መረጃ ምንጮች ከተሰበሰቡት የሲቪል ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ እስከአሁን ድረስ ማንነታቸውን በመለየት ለማረጋገጥ የተቻለው 45 ሲቪል ሰዎችን ብቻ ሲሆን፤ ነገር ግን የጉዳቱ መጠን ከዚህ ሊበልጥ እንደሚችል ምክንያታዊ ግምት ለመውሰድ ተችሏል፡፡

ምስክሮች በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ለኢሰመኮ ሲገልጹ፣ ለቀን ሥራ በጠዋት ከቤታቸው ወጥተው ድንገት ተኩስ ሲከፈት በአንድ ቦታ ተጠልለው የነበሩ 18 ሲቪል ሰዎች የተገደሉ መሆኑን፣ ቀበሌ 02 አካባቢ በተለምዶ ሚሊኒየም ተብሎ በሚጠራ ሰፈር አንድ የጠፋ አባልን ሲያፈላልጉ የነበሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች “በፍለጋው አልተባበሩም” ያሏቸውን 8 ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውን እንዲሁም 12 ባጃጆች በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መቃጠላቸውን ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ የዕድውኃ ከተማ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም. በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተካሄደ የተኩስ ልውውጥ ታጣቂዎች ከተማዋን ለቀው ከወጡ በኋላ ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ፣ እንዲሁም መንገድ ላይ የተገኙ ቢያንስ 15 ሰዎች (ሴቶችን ጨምሮ) በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከሕግ ውጭ የተገደሉ መሆኑን፤ በሌሎች ሁለት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ እንዲሁም በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ቋሪት ወረዳ፣ ወይበይኝ ቀበሌ፣ አብሥራ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ጥር 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ለወታደራዊ ቅኝት በአካባቢው የተሰማሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት ባደረጉት አሰሳ 6 ሲቪል ሰዎችን ከየቤታቸው አውጥተው ከሕግ ውጭ እንደገደሏቸው ምስክሮች ለኢሰመኮ አስረድተዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “በዚህ ግጭት በሁሉም ወገኖች በተለይም በየአካባቢው ነዋሪዎችና በሲቪል ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ሥቃይ እጅግ እየጨመረ በመምጣቱ ሁሉም ወገኖች ብቸኛው ዘላቂ መፍትሔ ሰላማዊ ውይይት መሆኑን ተቀብለው በቁርጠኝነት ይተገብሩት ዘንድ፣ እንዲሁም የተሟላ ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥና የተበደሉም እንዲካሱ አሁንም በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ብለዋል፡፡