የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እየተባባሰ የመጣውን የአማራ ክልል የትጥቅ ግጭትና የጸጥታ ችግር እንዲሁም በሰብአዊ መብቶች ላይ ያስከተለውን ተጽዕኖ ሲከታተል የቆየ እና ይህንኑም አስመልክቶ በነዋሪዎች እና በአካባቢው ላይ ያደረሰውንና የሚያደርሰውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ ሲቪል ሰዎች ለተጨማሪ ጉዳት እንዳይዳረጉ ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው። ሆኖም የጸጥታ ሁኔታው ከመሻሻል ይልቅ ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. አጋማሽ ጀምሮ እየተባባሰ በመምጣቱ ብዙ የክልሉ አካባቢዎች በግጭት ውስጥ መሆናቸውን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ሲቪል ሰዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን እና ሲቪል ሰዎችና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን፣ የትራንስፖርት እና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸውን፣ በቅርቡም የኢንተርኔት አገልግሎት በብዙ የክልሉ አካባቢዎች መቋረጡን፣ ነዋሪዎች በነጻነት ለመንቀሳቀስና ሥራቸውን ለመከወን መቸገራቸውን እንዲሁም የእንቅስቃሴ ገደቦች በአንዳንድ አካባቢዎች መጣላቸውን ለመገንዘብ ተችሏል። ግጭቱ ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በግጭትና በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ፣ እንዲሁም ከጎረቤት ሀገራት ግጭት በመሸሽ የተሰደዱ በክልሉ የሚገኙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችንም (ስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች እንዲሁም ፍልሰተኞች) ለከፍተኛ ችግር የሚዳርግ ነው።

ኢሰመኮ ከሚመለከታቸው የክልሉ እና የፌዴራል መንግሥት አካላት ጋር መነጋገርን ጨምሮ፣ በክልሉ እያከናወነ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል፣ እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅትም በአዋጅ ቁጥር 210/1992 (በአዋጅ ቁጥር 1224/2012 እንደተሻሻለው) አንቀጽ 6(12) መሠረት በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት ይቀጥላል።

ሁሉም ወገኖች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ እንዲሰጡ፣ ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ፣ የክልሉን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎች በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን ነዋሪዎችን ለበለጠ ጉዳት እና ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይዳርጉ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ በድጋሚ ያሳስባል። በተጨማሪም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 በሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ ተቀብላ ባጸደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ዕውቅና ያገኙ ሰብአዊ መብቶችንና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርሖችን በተለይም የጥብቅ አስፈላጊነት፣ በማናቸውም ሁኔታ የማይገደቡ መብቶችን የመጠበቅ፣ የተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነጻ መሆን መርሖችን ባከበረ መልኩ እንዲተገበር ያሳስባል።


በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ሊጠበቁ ስለሚገባቸው የሰብአዊ መብቶች፣ ድንጋጌዎች እና መርሖችን በሚመለከት ኢሰመኮ ከዚህ ቀደም ያወጣው ማብራሪያ ከዚህ በታች ተያይዟል፡፡