የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለያዩ ክልሎች ትምህርት የማግኘት መብት አፈጻጸምን በተመለከተ ባሉ አሳሳቢ ሁኔታዎች እና ሊወሰዱ በሚገባቸው የመፍትሔ እርምጃዎች ላይ ሐምሌ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ምክክር አካሂዷል። በውይይት መድረኩ ላይ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የክልል ትምህርት ቢሮዎች እንዲሁም የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ የሌሎች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በውይይቱ ላይ ትምህርት የማግኘት መብት በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ሕጎች መሠረት ያለው ጥበቃ፣ ተያያዥ የመንግሥት ግዴታዎች እንዲሁም ኢሰመኮ በተለያዩ ክልሎች የመብቱን አፈጻጸም በተመለከተ ያሰባሰበው መረጃ ቀርቧል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱና በቀጠሉ ግጭቶች፣ የተፈጥሮ አደጋዎች እና ተያያዥ መፈናቀሎች ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ሲሆኑ በርካታ ትምህርት ቤቶችም ከአገልግሎት ውጪ ሆነዋል። ለምሳሌ በአማራ ክልል 4178፣ በትግራይ ከልል 648፣ በኦሮሚያ ክልል 420፣ በሶማሊ ክልል 195፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 50፣ በጋምቤላ ክልል 40፣ በአፋር ክልል 26 እንዲሁም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል 8 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ኢሰመኮ ያሰባሰበው መረጃ ያመለክታል።
በተጨማሪም አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ማእከላዊ ኢትዮጵያ ያሉ ክልሎች ውስጥ የመምህራን ደመወዝ በወቅቱ እና በአግባቡ ባለመከፈሉ የመማር ማስተማር ሂደቱ በበርካታ ትምህርት ቤቶች ተስተጓጉሏል። በተመሳሳይ በሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ምክንያት በርካታ ተፈናቃይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል። ይህንን ተከተሎም ሕፃናት በተለይም ሴት ሕፃናት ከትምህርት መብት በተጨማሪ ያለ ዕድሜ ጋብቻን ጨምሮ ለሌሎች ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና ጥቃቶች ተጋላጭ መሆናቸው፣ ወደ ከተማ እየፈለሱና ለጉልበት ብዝበዛ እየተዳረጉ መሆኑ፣ ለተለያዩ ሱሶች እንዲሁም ሥነ-ልቦናዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች መጋለጣቸው በውይይቱ ተገልጿል።
የመድረኩ ተሳታፊዎች በተለያዩ ምክንያቶች የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት እና ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ለመመለስ እየተወሰዱ ስላሉ እና በቀጣይ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ተወያይተዋል። በዋነኝነት ችግሩን ለመፍታት በትጥቅ ግጭትም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት እንዲመለሱ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር፤ በግጭት ምክንያት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም በቂ በጀት የተያዘላቸውና በዕቅድ ውስጥ የተካተቱ መሆናቸውን ማረጋገጥ፤ ትምህርት ቤቶች በቋሚነት እስኪገነቡ ድረስ ጊዜያዊ የመማሪያ አማራጮችን ማዘጋጀት፤ ሕፃናት እና መምህራንን ጨምሮ የትምህርት ማኅበረሰቡ አባላት የሥነ-ልቦና እና ማኅበራዊ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻችት፤ በመፈናቀል ዐውድ ውስጥ ለሚገኙ ተማሪዎች የትምህርት ቤት የምገባ መርኃ ግብር ማስጀመር እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን መጠለያ ላደረጉ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ በማመቻቸት በመጠለያነት እያገለገሉ ያሉ የትምህርት ተቋማት የትምህርት አገልግሎት እንዲቀጥሉ ለማድረግ አዎንታዊ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ መግባባት ላይ ተደርሷል።
የኢሰመኮ የሴቶች፣ የሕፃናት፣ የአረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ፣ ትምህርት የማግኘት መብትን በማረጋገጥ ረገድ መንግሥት ግንባር ቀደም ባለግዴታ መሆኑን በአጽንዖት ጠቅሰው፣ በተለይም የ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን እየተቃረበ መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሠሩ እና በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ የሚገኘው የትምህርት መብት አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጠው የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።