የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሶሳ ዞን እና ከተማ አስተዳደር ሥር በሚገኙ የወረዳ ፖሊስ ጣቢያዎች ከሚያዚያ 2014 ዓ.ም. እስከ ታኀሣሥ 2015 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የተጠርጣሪዎች የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ክትትል አድርጓል። በክትትሉ በተለዩ ግኝቶች እና በቀረቡ ምክረ ሐሳቦች ዙሪያ ኮሚሽኑ መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. በባምባሲ ከተማ የቤንሻንጉል ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊና ምክትል ኃላፊ፣ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነር፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ሌሎች በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት አካሂዷል፡፡  

በውይይት መድረኩ ከቀረቡ አብይ ጉዳዮች መካከል፤  የሰብአዊ መብቶች መርሆችን መሠረት ያደረጉ አያያዞች፣ ልዩ ድጋፍና እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ተጠርጣሪዎች ሊደረግ ስለሚገባው አያያዝ፣  ተጠርጣሪዎች የተጠረጠሩበትን ወንጀል ያለመንገር ችግር እና በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ማሰር  ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም በፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ስላለው የአመራር ጣልቃ ገብነት፣ በሕግ ከተፈቀደው ጊዜ በላይ በጣቢያ ማቆየት፣ የዋስትና መብት መንፈግ፣ ተጠርጣሪዎችን በአደራ ከማስቀመጥ እና ከመቀበል ጋር በተያያዘ ስለሚፈጠሩ የመብት ጥሰቶች፣ የመጎብኘት መብት፣ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት፣ በፖሊስ ጣቢያ ውስጥ ተጠርጣሪዎች አቤቱታ ማቅረብ የሚችሉበት ልዩ ሥርዓት መዘርጋትን በተመለከተ እንዲሁም የተጠርጣሪዎች መረጃ አያያዝን የተመለከቱ እና ተያያዥ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች የክትትሉ ዋና የትኩረት ነጥቦች ከሆኑት መካከል ናቸው፡፡ የተጠርጣሪዎች ማረፊያ ክፍሎች ደረጃ፣ መጸዳጃ ቤቶች፣ የጽዳትና የግል ንጽሕናን የተመለከቱ ጉዳዮች፣ ምግብ፣ ውሃ፣ ሕክምና እና የመሳሰሉት መሠረታዊ አገልግሎቶች የማግኘት መብቶችም በውይይቱ ተዳሰዋል፡፡

ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክትትሉ የተለዩ ግኝቶችን እንደሚቀበሏቸው ገልጸው እንደ ፖሊስ ላሉ ተቋማት አነስተኛ በጀት የመመደብ ሁኔታ መኖሩ፤ የፖሊሶችና ዐቃቤ ሕጎች መሰላቸት፣ የተነሳሽነትና የቁርጠኝነት ማነስ፣ የቅንጅታዊ አሠራር አለመኖር እንዲሁም የፖለቲካ አመራር ጣልቃ ገብነት መኖሩ፤ የጸጥታ ችግርና በፍትሕ ተቋማት የተዘረጋው የክትትልና ቁጥጥር ሥርዓት መላላት ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት መባባስ ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡  

እነዚህን ሁኔታዎች ከማሻሻልና በኮሚሽኑ የሚሰጡ ምክረ ሐሳቦችን ከመፈጸም አኳያ በሰው አካል ላይ ጉዳት ያደረሱና የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በፈጸሙ ከ20 በላይ የፖሊስ አባላት ላይ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን፤ የወረዳና ዞን ፖሊስ ጣቢያዎችን ለመገንባት ከተለያዩ በጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውንና በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ የማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰዳቸውን ጠቁመዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የኢሰመኮ አሶሳ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጉርሜሳ በፉጣ ነባር ሕጎች እንዲሻሻሉ በማድረግ፤ የሰብአዊ መብቶች ግንዛቤዎችን በመፍጠር፣ የፖሊቲካ አመራሮችን በማወያየት የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ እንዲጠናከር እንዲሁም የዜጎችን ሰብአዊ መብቶች በማክበር እና በማስከበር ረገድ የፍትሕ አካሉ ቀዳሚ ኃላፊነት አለበት ብለዋል። አክለውም በተጠርጣሪዎች ላይ ድብደባና ኢሰብአዊ ድርጊቶችን በሚፈጽሙ የጸጥታ አካላት ተገቢው ምርመራ ተካሂዶ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፣ ቅንጅታዊ አሠራሮች እንዲጠናከሩ እና የፖሊስ የአባላቱን  ሥነ ምግባርና የተጠርጣሪዎች መረጃ አያያዝን ለማሻሻል በጋራ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡