የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ቁጥራቸው ከ160 በላይ የሚሆኑ አካል ጉዳተኞች በኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት በአካል ተገኝተው ያቀረቡትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ቅሬታ ተቀብሏል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ካለው የንግድ ቤቶች የማፍረስ ሂደት ጋር በተገናኘ የንግድ ቤቶቻቸው ያላግባብ እንዲፈርሱ መደረጉን፣ ንብረታቸው መወሰዱን እንዲሁም ቅሬታቸውን ለማቅረብ በሄዱባቸው የመንግሥት ተቋማት በጸጥታ አካላት ማዋከብ እና እንግልት የደረሰባቸው መሆኑን ለኮሚሽኑ አስረድተዋል።

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ ኮሚሽኑ ቅሬታቸውን ተቀብሎ የክትትል እና የምርመራ ሥራዎችን በአፋጣኝ እንደሚጀምር እና ግኝቶቹንም እንደሚያሳውቅ ገልጸዋል። ኮሚሽነር ርግበ አክለውም ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው የንግድ ቤቶችን የማፍረስ ሂደት ሕጋዊ ሥርዓትን መከተልና እርምጃው በተለይ በአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ ከግንዛቤ በማስገባት መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።