የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በ2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በአሥራ አንድ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች በሚገኙ የተጠርጣሪ ማቆያዎች ላይ ከታኅሣሥ 13 እስከ ታኅሣሥ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. እና ከግንቦት 5 እስከ ግንቦት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል አድርጓል። እንዲሁም በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ሥር በሚገኙ 5 ማረሚያ እና ማረፊያ ቤቶች ማለትም በፌዴራል ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት (ቃሊቲ)፣ በቃሊቲ ሴቶች ማረሚያ ቤት፣ በዝዋይ ማረሚያ ቤት፣ በድሬዳዋ ማረሚያ ቤት እና በፌዴራል የቀጠሮ ማረፊያ ቤት ላይ ከሕዳር 13 እስከ ሕዳር 21 ቀን 2015 ዓ.ም. እና ከግንቦት 23 እስከ ግንቦት 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሁለት ዙር የአፈጻጸም ክትትል አካሂዷል። በአፈጻጸም ክትትሉ የለያቸውን ግኝቶች ለማሳወቅና የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከፌዴራል እና ከከተማ አስተዳደሩ ከተውጣጡ የፍትሕ ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ጋር ሐምሌ 3 እና 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

በሁለቱ የውይይት መድረኮች የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና እና ምክትል ኮሚሽነሮች እና የአዲስ አበባ አስራ አንዱ ክፍለ ከተሞች የወንጀል ምርመራ ምክትል ዳይሬክተሮች ተገኝተዋል። በተጨማሪም ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊና ዋና ሬጅስትራር፣ ከፌዴራል የመጀመሪያ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የወንጀልና ፍትሐብሔር አስተባባሪ ዳኞች፣ ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ እና መከላከል ከፌዴራል ፍትሕ ሚኒስቴር እና ከአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች፣ ከአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናት እና ማኀበራዊ ጉዳዮች ቢሮ፣ ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰብአዊ መብቶች ማዕከል፣ ከሕግ ባለሞያዎች ለሰብአዊ መብቶች እና ከፍትሕ ለሁሉም ሲቪል ማኀበር ድርጅቶች፣ ቢሮ የተውጣጡ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

በውይይቱ የፖሊስ ጣቢያዎችንና ተጠርጣሪ ማቆያዎችን በተመለከተ በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጭ መያዝና ብርበራ መፈጸምን ለማስቀረት ለፖሊስ አባላት ዕለታዊ መመሪያ የሚሰጥ መሆኑ እና በሁሉም የክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች ለፖሊስ አባላት በሰብአዊ መብቶች ላይ ያተኮረ ስልጠና መሰጠቱ በበጎ እርምጃዎች ተጠቅሰዋል፡፡ እንዲሁም የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በፈጸሙ የፖሊስ አባላት ላይ የተወሰደ የዲሲፕሊን እርምጃ መኖሩ፤ በልደታ፣ በአዲስ ከተማ፣ በአራዳ እና በኮልፌ ቀራንዮ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያዎች ለተጠርጣሪዎች ማቆያ የሚሆኑ አዲስ ሕንፃዎች መገንባታቸው እንደ መልካም ተሞክሮ በክትትሉ የተለዩ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች በተደረገ ክትትል ለታራሚዎች የተፈቀደው የምግብ በጀት ከ22 ብር ወደ 35 ብር ከፍ መደረጉ እና ተቋርጦ የነበረው ታራሚዎች በመንግሥት ጤና ተቋማት በሪፈር በነጻ ሲሰጥ የቆየው የሕክምና አገልግሎት መቀጠሉ ከሥርዓታዊ ለውጦች ጋር በተገናኘ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በኮሚሽኑ ምክረ-ሐሳብ መሠረት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በፈጸሙ የማረሚያ ቤት ፖሊስ አባላት ላይ እርምጃዎች መወሰዳቸውና የሕክምና እና መድኃኒት አቅርቦት መሻሻሉ ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም በሁሉም ማ/ቤቶች ሥር በሚገኙ ዞኖች ሕግና ደንቦችን የያዙ ማስታወቂያ ሰሌዳዎች መኖራቸው፣ የእስረኞች መብትና ግዴታዎች፣ አዋጆችና የአመክሮ መመሪያዎች፣ የዲሲፒሊን አፈጻጸም መመሪያ በየቤተመጽሐፍት እንዲኖር መደረጉ፣ የውሃ አቅርቦት መሻሻል እንዲሁም የቤተሰብ ጉብኝት ቀናት መጨመሩ በአወንታዊ መሻሻል የተጠቀሱ ናቸው፡፡ የተጀመሩ የማቆያ ቤቶች ግንባታ መጓተት፣ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታራሚዎችን ለአካለ መጠን ከደረሱ ታራሚዎች በግቢ ለይቶ አለመያዝ፣ የአእምሮ ሕመም ያለባቸው ታራሚዎች በቂና ተመጣጣኝ የሕክምና አገልግሎት አለማግኘታቸው ተጠቁሟል፡፡ ከታራሚ እናቶቻቸው ጋር በማረሚያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሕፃናት ትምህርትና እንክብካቤ የማያገኙ መሆኑ እንዲሁም የጉዳይ አስፈጻሚዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የሕግ ክርክር ክትትል ላይ ክፍተቶች መኖራችው በማረሚያ ቤቶች እንደተግዳሮት የተለዩ ጉዳዮች ናቸው።

በሌላ በኩል በፖሊሰ ጣቢያዎች በሪፈራል የሚሰጥ የነጻ ሕክምና አገልግሎት አለመኖሩ፣ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ተጠርጣሪዎችን በግቢ እና በማደሪያ ክፍል ለይቶ አለመያዝ፣ ተጠርጣሪዎች ከቤተሰብ ጋር የሚገናኙበት ስልክ አገልግሎት አለመኖር፣ ለሴት ተጠርጣሪዎች የንጽሕና ቁሳቁሶችን አለማቅረብ እና የምግብ አቅርቦት በጀት እጥረት መኖሩ በኢሰመኮ የተለዩ ክፍተቶችና መፍትሔ ያላገኙ ምክረ ሐሳቦች ናቸው፡፡ ለኮሚሽኑ በቀረቡ አቤቱታዎች ላይ ተመሥርቶ በተደረጉ ምርመራዎች የዘፈቀደ እስር መኖር፣ በፍርድ ቤት የዋስትና መብት የተከበረላቸው ተጠርጠሪዎች በድጋሚ በተመሳሳይ ወንጀል በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ተደጋግመው እንዲያዙ መደረጉ እና ሕዝባዊ በዓላት እና የተለያዩ የአደባባይ ኹነቶች ሲኖሩ በርካታ የጎዳና ተዳዳሪዎች እና መታወቂያ ያልያዙ ግለሰቦች ከሕግ ውጭ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው በ2015 ዓ.ም. እንደክፍተት የተለዩ ግኝቶች ናቸው፡፡

ተሳታፊዎች በበኩላቸው በክትትል ሥራው የታዩ አበረታች ውጤቶችን ለማስቀጠል እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡ በቀረቡት ምክረ ሐሳቦች መሠረትም ከእናቶቻቸው ጋር በማ/ቤት ውስጥ ያሉ ሕፃናት አያያዝ እና በፖሊስ ጣቢያዎች የሚገኙ ተጠርጣሪ ሴቶች ንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦት አለመኖር ጋር በተያያዘ ሳይቀረፉ የቆዩ መሠረታዊ ክፍተቶችን በተመለከተ የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኀበራዊ ቢሮ በሚቀርብለት ጥያቄ መሠረት እልባት እንደሚሰጣቸው የጋራ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በመጨረሻም በአምስቱ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች እና አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በ2015 ዓ.ም. ያልተፈጸሙትንና አዲስ የተለዩ ክፍተቶችን ለማሻሻል በአፋጣኝ፣ በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚፈጸሙ ምክረ ሐሳቦችን በመለየት የአንድ ዓመት የጋራ የድርጊት መርኃ ግብር ተቀርጿል።

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ያረጋል አደመ በታራሚዎች አያያዝ ዙሪያ የሚስተዋሉ ጉድለቶች እንዳሉ ገልጸዋል። ጉድለቶችን አርሞ ደረጃውን የጠበቀ የማረሚያ ቤት አገልግሎት ለመስጠት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በየጊዜው በሚያደርገው ክትትል የሚያቀርባቸው ምክረ ሐሳቦች ታራሚዎችን ሕግ አክባሪና አምራች ዜጎች አድርጎ ወደ ማኀበረሰቡ መልሶ ለመቀላቀል ለሚደረገው ጥረት እጅጉን እንደሚረዳቸው አብራርተዋል፡፡ በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሀሰን ነጋሽ በማጠቃለያ ንግግራቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በፖሊሰ ጣቢያዎች የሚያደርገው ክትትል የተጠርጣሪዎችን ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል የጎላ አስተዋጽዖ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በውይይት መድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት “በሀገራችን በሕግ ጥበቃ ሥር የሚገኙ ሰዎች ሰብአዊ ክብራቸው ተጠብቆ የመያዝ ሁኔታን ለማሻሻል እና ታራሚዎች በቆይታቸው ታርመውና ታንጸው እንዲወጡ ለማስቻል በሚሠሩት ሥራዎች በተቋማቱ መካከል ያለው ግንኙነት በትብብርና በመደጋገፍ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት” ብለዋል፡፡