የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር ክልል ሰመራ ፖሊስ ጣቢያ፣ ሎጊያ እና ሚሌ የፖሊስ ማቆያዎች እና በክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ስር በሚገኙት የአውሲረሱ (ፈንቲረሱ፣ ኪልቢትረሱ) እና ገቢረሱ ማረሚያ ቤቶች ላይ ከግንቦት 15 እስከ 22 ቀን 2014 ዓ.ም. የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል አድርጓል። ኮሚሽኑ ለክትትል ሥራው ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ እንዲሁም ሀገራዊ የሰብአዊ መብቶች መርሆች ላይ ተመርኩዞ ከተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎች ጋር የተናጠልና የቡድን ውይይት፣ ከፖሊስ ጣቢያና የማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎች ጋር ቃለ መጠይቆችን እንዲሁም ምልከታ አድርጓል።

ኢሰመኮ በክትትሉ በተለዩ ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች ዙሪያ የክልሉ ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል፣ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ተወካይ፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚደንት፣ ፍትሕ ቢሮ ምክትል ኃላፊ እና ከማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች በተገኙበት ከጥቅምት 22 እስከ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰመራ ከተማ ውይይት አካሂዷል። 

ለተከታታይ ሁለት ቀናት በቆየው ዝግጅት በፖሊስ ጣቢያዎች እና በማረሚያ ቤቶች ላይ በተካሄደው ክትትል የተለዩ መልካም ጎኖች እና ትኩረት  የሚሹ ክፍተቶች ቀርበዋል፡፡ ተጠርጣሪዎች ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቸው ጋር ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር በሳምንት ሁሉም ቀናት መገናኘታቸው ክትትል በተደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች ከተስተዋሉ መልካም ጎኖች ውስጥ ተጠቃሽ ነው።

በተመሳሳይ በማረሚያ ቤቶች ታራሚዎች ወደ ማረሚያ ቤት ሲገቡ የግል ማኅደር ተከፍቶላቸው ስማቸው፣ አድራሻቸው እና የእስር ትዕዛዙን ያስተላለፈው ፍርድ ቤት እና የፈጸሙት ወንጀል የሚመዘገብ መሆኑ፣ አማርኛ ቋንቋን የማይናገሩ ታራሚዎች በማረሚያ ቤቱ ሠራተኞች እና ታራሚዎች በኩል በሚረዱት ቋንቋ አስፈላጊውን መረጃ እንዲያገኙ  ጥረት የሚደረግ መሆኑ፣ ወደ ፍርድ ቤት፣ የሕክምና እና ሌሎች ተቋማት ለማጓጓዝ ካልሆነ በስተቀር ታራሚዎች በካቴና የማይታሰሩ መሆኑ በመልካም ምሳሌነት ተነስተዋል። 

በሌላ ጎን በፖሊስ ጣቢያዎች ሰዎችን ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዝ፣ በሰመራ እና ሎጊያ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ለፖሊስ በነጻነት ቃል እንደማይሰጡ እንደሁም ማስፈራራት እና ዛቻ እንደሚደርስባቸው፣ አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎች በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ፣ የተጠርጣሪዎች ማደሪያ ክፍሎች ጠባብ መሆን፣ የመጸዳጃ እና የንጽሕና መጠበቂያ ቤቶች አለመኖር እና በተለይም የሎጊያ ፖሊስ ማቆያ ለሴት ተጠርጣሪዎች የተለየ ክፍል የሌለው በመሆኑ ከክፍል ውጪ በረንዳ ላይ እንዲያድሩ መደረጉ ትኩረት ከሚሹ ክፍተቶች መካከል ናቸው።

በማረሚያ ቤቶች ታራሚዎችን ወደ ፍርድ ቤት፣ የሕክምና እና ሌሎች ተቋማት ለማጓጓዝ በቂ ተሽከርካሪ አለመኖር፣ የፖሊሶች ክፍያና ጥቅማ ጥቅም አነስተኛ መሆን እና የሰው ኃይል እጥረት መኖር፣ ታራሚዎች ወደ ማረሚያ ቤቶቹ ሲገቡ የተቋማቱን ዓላማ እንዲሁም ለታራሚዎች በሕግ የተሰጡ መብቶች እና ግዴታዎች በማረሚያ ቤቶቹ አስተዳደር በኩል አለመገለጽ መሻሻል ከሚገባቸው ክፍተቶች ውስጥ ተካተዋል። በተጨማሪም ተላላፊ በሽታ ያለባቸውን እና ዕድሜን መሰረት በማድረግ ለይቶ ማቆያ ክፍል አለመዘጋጀቱ፣ የቀለም ትምህርት የሚሰጡ መምህራን ታራሚዎችን ለማስተማር በፈለጉ ጊዜ ብቻ የሚመጡ መሆኑ እና ማረሚያ ቤቱም በዚህ ረገድ በመምህራን ላይ ቁጥጥር አለማድረጉ በመድረኩ ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የዝግጅቱ ተሳታፊዎች የቀረበው ሪፖርት ያለውን ችግር ያመላከተ መሆኑን እና ተገቢውን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የሚገልጹ ሃሳቦች አንፀባርቀዋል፡፡ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው የአፋር ክልል በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት መጠነ ሰፊ ጉዳት የደረሰበት እና በርካታ ቁጥር ያለውን ተፈናቃይ የሚያስተናግድ ክልል መሆኑን ኮሚሽኑ እንደሚረዳ፤ ኮሚሽኑም ተቋማቱን ለመደገፍ ክትትልን ጨምሮ የተለያዩ የሽግግር ጊዜ ፍትሕ እና የአቅም ግንባታ ሥራ የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢሰመኮ የሰብአዊ መብቶች የክትትል እና ምርመራ ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ በመዝጊያ ንግግራቸው ባለፈው ግንቦት ወር ላይ በኮሚሽኑ የክትትል ሥራ  ግኝቶች መነሻነት የተሰጡ ምክረ ሃሳቦች በከፊል መፈጸማቸው መገለጹ እጅግ አበረታች ጅምር መሆኑን ገልጸው በተለይም የሴቶች ማቆያ ቦታዎችንና የንጽሕና አጠባበቅን አስመልክቶ ለማሻሻል የታየው ቁርጠኝነት አበረታች ነው ብለዋል።

በዝግጅቱ ማብቂያ በቀጣይ ተግባራዊ የሚደረጉ ምክረ ሃሳቦችን በታቀደው ጊዜ ለመፈጸም እና ኮሚሽኑ በአፈጻጸሙ ላይ በቅርበት የክትትልና የውትወታ ሥራውን እንዲቀጥል መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡