የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ሥራ ክፍል የ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት አፈጻጸሙን እንዲሁም የ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት ዕቅድ ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅና አብሮ የመሥራት ጥሪ ለማቅረብ መስከረም 10 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል፡፡

በውይይቱ ወቅት በተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ አገልግሎት ሰጪ አካላት እና የግንዛቤ እጥረት ባለባቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች፤ አካል ጉዳተኞችን እና አረጋውያንን በተመለከተ የሚሠሩ ሥራዎች ብዙውን ጊዜ እንደ ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ሳይሆን እንደ በጎ አድራጎት ሥራ የሚቆጠሩ መሆኑ በተሳታፊዎች ተነስቷል። በተጨማሪም ለአረጋውያን ሰብአዊ መብቶች የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛነት፣ የኢትዮጵያ የሕንጻ አዋጅ ቁጥር 624/2001 የአፈጻጸም ክፍተት የሚታይበት መሆኑ ተገልጿል፡፡ በረቂቅ ደረጃ ያለው የአካል ጉዳተኞች ጥቅል ሕግ መዘግየት፣ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የአካል ጉዳተኞች መብቶች ራሱን የቻለ ድንጋጌ የሌለውና የሚሰጠው ጥበቃም በቂ አለመሆን እና አካል ጉዳተኛ ለሚለው ቃል ግልፅ ሀገራዊ ትርጓሜ አለመኖሩን ጠቅሰው፤ ኮሚሽኑም እነዚህን ጉዳዮች በአትኩሮት ሊመለከታቸው እና ሊሠራባቸው የሚገባ መሆኑን ተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡

የኢሰመኮ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች ኮሚሽነር ርግበ ገብረሐዋርያ የሥራ ክፍሉ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶችን በተመለከተ ከበጀት ዓመት ዕቅዱ በተጨማሪ የተለያዩ አቤቱታዎችን መሰረት ያደረጉ ክትትል ሥራዎች እንደሚያከናውን ገልጸዋል። አክለውም በበጀት ዓመቱ ዕቅዶች ላይ በመንፈቅ ዓመት ክለሳ ሲካሄድ እንደአስፈላጊነቱ ለውጦች እንደሚደረጉ ለተሳታፊዎች አስረድተዋል፡፡ ኢሰመኮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን መብቶች መከበር እና መጠበቅ በጋራ የሚሠራበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እና ግብአት ለመሰብሰብ ይህን መሰል መድረኮች ፋይዳቸው የጎላ ነው ሲሉ ኮሚሽነር ርግበ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የዝግጅቱ ተሳታፊዎች በውይይቱ የተለዩትን ክፍተቶች ለማሻሻል በውትወታ ሥራዎች ላይ ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ ለመሥራት መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡